የካቲት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የካቲት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በ ንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ “አስመጪዎቹ ታክስን በሚመለከቱ ለወጡ ሕጎች ተገዢ ባለመሆን፣ የሚያስመጧቸውን ዕቃዎች ከዋጋ በታች ደረሰኝ በመቁረጥ፣ ያለ ደረሰኝ በመሸጥ፣ በሚቆርጡት ደረሰኝ ላይ የገዢን ማንነት አለመጥቀስ፣ ግዢን በሒሳብ ውስጥ አለማካታት፣ ከንግድ ትርፍ የሚገኝን ገንዘብ መሬት ውስጥ መቅበር፣ ወደ ውጭ አገር ማሸሽ፣ በስቶክ ካርድ ላይ ገቢና ወጪን አለመመዝገብ፣ ስቲከሮችን በማስመጣት ኦርጂናል ባልሆነ ዕቃ ላይ ኦርጂናል አስመስሎ መለጠፍ፣ ከጉምሩክ ቀረጥ ለማምለጥ ኦርጂናል የሆኑትን ዕቃዎች እዳንዳልሆኑ የሚገልጽ ስቲከር በመለጠፍና ከቀረጥ በኋላ ኦርጂናል መሆናቸውን በማሳወቅና በሌሎችም ሕገወጥ መንገዶች ማጭበርበር በመፈጸም በአገር፣ በዜጎችና በንግድ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ” መሆኑን መንግስት መናገሩን ሪፖርተር ዘግቧል።
የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ በአስመጪነትና በላኪነት የሥራ ዘርፍ የውጭ ባለሀብቶች እንዳይሳተፉ መደረጉ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ እርስ በርሱ ተወዳዳሪ እንዲሆንና ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሆንም፣ ነጋዴዎች ለምን በሕጋዊ መንገድ ሠርተው መክበር እንዳማይፈልጉ ግራ እንዳሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
ነጋዴዎች በበኩላቸው የችግሩ መንስዔ ‹‹የአስፈጻሚውና ሕገወጥ አስመጪዎች እከክልኝ ልከክልህ›› አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕገወጥ ባለሀብቱን ወይም አስመጪውን ባለሥልጣኑ አብጠርጥሮ እንደሚያውቀውና የጉምሩክ ሥራውን በተላላኪ በኩል እንዴት እንደሚያስፈጽም ከኃላፊዎችና ከባለሥልጠናቱ የተሰወረ አለመሆኑን ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡ ሕጋዊ ነጋዴው ግን በመዶሻ እየተኮረከመ ሲጮህ የሚደርስለት እንደሌለም አክለዋል።
‹‹ራስህ ታጥበህ ስትበላ ነው እጅህን ታጠብ ማለት የምትችለው›› በማለት በመንግስት በኩል ለሕግ ተገዢ ሆኖ የማስፈጸም ችግር መኖሩንና ከብልሹ አሠራር በፀዳ ሁኔታ መስተናገድ እንደማይቻል ያስረዱት አስመጪዎች፣ ነጋዴዎች መፍትሔ ማጣታቸውን መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ራሱን መፈተሽ እንዳለበት ነጋዴዎቹ ተናግረው፣ ጊዜያቸው የሚያልፍባቸው ምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ከሌሎቹ ተለይተው የሚገቡበት አሠራር እንዲፈጠር፣ ጊዜ የሚወስደው የቀረጥ ሥርዓት እንዲፋጠንና ከሥር ያሉ ኃላፊዎች አሠራር እንዲፈተሽ ጠይቀዋል፡፡ ስም እየጠቀሱ ቢያስረዱ ደስተኛ እንደሚሆኑ ነጋዴዎች፣ የነገ ተጠቂ እንደሚሆኑ ስለሚያውቁ ግን በደፈናው መናገርን መምረጣቸውን አስረድተዋል፡፡