(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 11/2018) የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ዛሬ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወደ ወህኒ ለመጋዝ ምክንያት የሆነባቸው ከቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት ሙአመር ጋዳፊ መንግስት ለምርጫ ዘመቻ በሚሊየን ዮሮ የሚቆጠር ገንዘብ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ተቀብለዋል በሚል ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 ለተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊየን ዩሮ ተቀብለዋል በሚል የተወነጀሉት ሳርኮዚ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይቷል።
የምርመራው ሒደት ይበልጥ ትኩረት የሳበው የፈረንሳይና የሊባኖስ ዜጋ የሆነው ዚያድ ታኪ ድሊን የተባለ ነጋዴ ከሊቢያ የተላከ 5 ሚሊየን ዮሮ በጥሬው የያዘ ሻንጣ ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ሳርኮዜ ለጠቅላይ ኢታማጆር ሹማቸው አስረክቤያለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ዛሬ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፓሪስ ወደሚገኘው አንድ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውም ታውቋል።