ትናንት ሀሙስ እስራኤል በፈጸመችው ግዙፍ ጥቃት የተቆጣችው ኢራን ፣“ሶሪያ ራሷን የመከላከል መብት አላት” ስትል አስታወቀች።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 03 ቀን 2010 ዓ/ም) እስራኤል በትናንቱ ጥቃት ሶሪያ ውስጥ ያሉ የኢራን ወታደራዊ ቤዞችን እንዳውደመች ነው የገለጸችው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ባወጣው መግለጫ የእስራኤል ድርጊት የሶሪያን ሉዓላዊነት የጣሰ ነው በማለት የእስራኤልን ድርጉት አውግዟል። እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ ጥቃቱ ላለፉት አስር ዓመታት እስራኤል ሶሪያ ምድር ላይ ከፈጸመችው ጥቃት ሁሉ የከፋ ነው ። እስራኤል ይህን ጥቃት የፈጸመችው በጎላን ተራራ ባለው ወታደራዊ ይዞታዋ ላይ 20 ሮኬቶች መተኮሳቸውን ተከትሎ ነው።
እስራኤል የሮኬት ጥቃቱን የፈጸሙት ኢራናውያን እንደሆኑ ስትከስ፣ ቴህራን ግን እሷ ስለመሆኗ ወይ አላረጋገጠችም፣አለያም አላስተባበለችም። ኢራን በሶሪያ “እንደ አማካሪ” በማለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አስፍራለች።
እንዲሁም በሺህዎች የሚቆጠሩ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ሚሊሻዎች ከሶሪያ መንግስት ጎን በመሆን አማጺ ኃይሎች ጋር እየተፋለሙ ይገኛሉ።
በጎላን ተራራ ለተተኮሰባት ሮኬት ትናንት የጀት ጥቃት በመፈጸም አጸፋውን የመለሰችው ቴል አቪቭ፦” ተዋጊ ጄቶቿ በሶሪያ ውስጥ ያሉ የኢራን ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን ሙሉ በሙሉ ማውደሟን አስታውቃለች።