ጥር ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፎርቹን ሳምንታዊ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ ሆቴሉ የሚፈርሰው በአካባቢው ለሚሰራ የ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ተብሎ ነው።
የ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገዷን ለመስራት 400 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል መባሉንም ጋዜጣው አስነብቧል። ሆቴሉ ለልማት ፕሮግራም ተብሎ እንዲፈርስ ከአስር ቀን በፊት በቂርቆስ ክፍለ-ከተማ ትዕዛዝ መውጣቱ ተመልክቷል።
ባለፈው ስርዓት የመንግስት እንዲሆን ተደርጎ በዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች ኢንተርፕራይዝ ስር ሲተዳደር የቆየው መስቀል ፍላወር ሆቴል፤ ሁዋላ ላይ ለግል ባለሀብቱ እንዲመለስ ተደርጎና እንደ አዲስ ስራውን ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ሆቴሉ ማፍረስ ያስፈለገው፤ ለ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገዷ- ማዞሪያ አደባባይ ለመስራት እንደሆነ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የኮንስትራክሽንና የቁጥጥር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ኪዳኔ ተናግረዋል።