(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 3/2010)
በኢትዮጵያ የሕወሃት አገዛዝ ከስልጣን እንዲወርድ የሚካሄደው ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች መቀጠሉ ተነገረ።
በሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች በመገደላቸው ተቃውሞው በተለያዩ ከተሞች እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።
የሕወሃት አጋዚ ወታደሮች ተቃውሞዎቹን ለመቆጣጠር እንደተሳናቸውም ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በቋንቋና ብሔር ላይ የተመሰረተው የሕወሃት ፌደራሊዝም ውጤቱ ግጭትና ትርምስ መሆኑን እያመላከተ ይገኛል።
ግጭቶችና ጥቃቶች አንዴ በስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ሌላ ጊዜ ደግሞ በዩኒቨርስቲዎች የሚከሰቱት ብሔርን ከብሔር በመለየትና ቋንቋን መሰረት በማድረግ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች እንዲለያዩ ግጭቶችን የሚያራግበው ሕወሃት አሁን የሚይዘውንና የሚጨብጠውን አጥቷል።
ሰሞኑን በአዲግራት ዩኒቨርስቲ የተገደሉትን ተማሪዎች መነሻ ያደረገው ተቃውሞ በሌሎችም ዩኒቨርስቲዎችም ተዛምቷል።
ከዩኒቨርስቲዎች ደግሞ ወደ ከተሞች በመስፋፋት ተቃውሞው ብዙ አካባቢዎችን እያዳረሰ ነው የሚገኘው።
ከተማሪዎቹ መገደል ጋር ተያይዞ በሰሜን ወሎ ውርጌሳ ከተማ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ደቡብ ወሎ ውጫሌ ከተማ ደርሷል።
በውርጌሳም ሆነ ውጫሌ የተነሳው ተቃውሞ ልጆቻችን ከትግራይ ዩኒቨርስቲዎች ሳይመለሱ ተሽከርካሪም ሆነ ማንኛውም እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል ባይ ናቸው።
በዚሁም አንድ ሰላም ባስ በተቃዋሚዎቹ ጉዳት ሲደርስበት ሌሎች ተሽከርካሪዎች ደግሞ እንዲታገቱ ተደርገዋል።
በአምቦ ከተማም ተቃውሞ ተቀስቅሶ ቄሮዎች ወደ ከተማዋ የሚያስገቡና የሚያስወጡ መንገዶችን መዝጋት ጀምረዋል።
በጉጂ ጎሮም ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ተቃውሞ እያሰማ ይገኛል።
በምስራቅ ሀረርጌ ጨለንቆም 18 ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት መገደላቸውን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መንገሱ ነው የተሰማው።
የመከላከያ ሰራዊት ተቃውሞ በተነሳባቸው አካባቢዎች ቢንቀሳቀስም ተቃውሞውን ግን ማብረድ አልቻለም።
ተቃውሞ በተነሳባቸው አካባቢዎች ተኩስ እዚህም እዚያም ቢሰማም “ወያኔ” ሌባ፣ሕወሃት ከስልጣን ይውረድ የሚሉ ተቃውሞዎች ግን በየአካባቢዎቹ መስተጋባታቸው ቀጥሏል።