(ኢሳት ዲሲ–ጥር 24/2011)ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጡ።
የከፍተኛ ትምህር ተቋማት ተማሪዎች ራሳቸው ከፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያነት እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ ወንጀል ሰርቶ በመንግስትም ተረጋግጦ ያልታሰረ ሰው የለም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የክልል ጥያቄ ህገመንግስታዊ ቢሆንም የክልል ስያሜ ማግኘት ብቻውን መፍትሄ አይሆንም ሲሉ ገልጸዋል።
በቅርቡ የጸደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን የተቋቋመው ክልል ለመሸንሸን አይደለም ብለዋል።
ኮንትሮባንድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እያናጋው እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት በሰጡ ማብራሪያ ላይ አንስተዋል።
ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኢኮኖሚ ፈተናዎች አንስቶ በሰላምና መረጋጋት ሀገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች መዳሰሳቸው ነው የተገለጸው።
የከፍተኛ ትምህር ተቋማት ተማሪዎች የፖለቲካ ነጋዴዎች የትኩረት ሃይሎች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጠቀሚያ ባለመሆን የመጀመሪያው ሃላፊነት የሚቀድመውም በተማሪዎቹ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፖለቲካ አጀንዳውን በትምህርት ተቋማት ውስጥ በማስገባት በተማሪዎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት የሚፈጥር የፖለቲካ ፓርቲ በዓለም ላይ በብቸኝነት ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንዱ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋል ያልተቻለበትን ምክንያት የተመለከተ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ በመንግስትም ተረጋግጦ ያልታሰረ ሰው የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ልዩነቱ በመንግስት የታሰረና የሚቀለብ እስረኛ መሆንና በራሱ ጊዜ ራሱን ያሰረ እስረኛ ነው ብለዋል።
በስም ባይጠቅሱም አንዳንድ ክልሎች ወንጀለኞችን እንዳላገኟቸውና እያፈላለጓቸው እንደሆነ መግለጻቸውን ጠሚኒስት አብይ አንስተዋል።
የክልል ጥያቄ በተለይም በደቡብ የኢትዮጵያ እየተበራከተ መምጣቱን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጥያቄው ህገመንግስታዊ እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥያቄውን መመለስ ግን ምላሽ አይሆንም ብለዋል።
ከ10 በላይ ዞኖች የክልል ጥያቄ አቅርበዋል ክልል የሚለውን ስያሜ በማግኘት ግን የሚፈታ ችግር የለም ነው ያሉት።
ሉዓላዊ ሃገር እንጂ ሉዓላዊ ክልል የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይጠና ጥቅምና ጉዳቱ ሳይፈተሽ ጥያቄው ስለቀረበ ብቻ ክልል መሆን መፍትሄ አያመጣም ብለዋል።
በፓርላማው የጸደቀው የአስተዳደር ወሰንናን የማንነት ኮሚሽን የክልል ሽንሸና ሊያካሂድ የተቋቋመ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በዛሬው የምክር ቤት ውሎ የኢኮኖሚ ጉዳዮችም ተነስተዋል።
የኮንትሮባንድ ንግድ ከፍተኛ ፈተና ደቅኖብናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ።
ኢኮኖሚያችንን እያናጋ ነው ሲሉም የአደጋውን ጥልቀት አሳይተዋል።
የኮንትሮባንዲስቶችን የገንዘብ ምንጭ ለማድረቅ፣ ከጎረቤት አገራት ጋር ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት እየተዋጋነው ነው ብለዋል።