ጥር 25 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ህጉ የህዝብን መብቶች አላግባብ ለማፈን በጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለፀ
የመንግስታቱ ድርጅት ገለልተኛ የሰብኣዊ መብት የባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ያለአግባብ በመወንጀልና እስራት በመፍረድ የፀረ ሽብር ህጉን በመጠቀም የህዝብን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማፈን መንግሰት የሚፈፅመዉን ተግባር አውግዘዋል።
“የመንግሰት ባለስልጣኖች የሚፈፅሟቸዉን የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመርና በማሳወቅ ሊኖራቸዉ የሚገባዉን ተጠያቂነት በማስገንዘብ ረገድ ጋዜጠኞች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ። ህጋዊ ተግባራቸዉን ስላከናወኑ ስንኳንስ በአስከፊ ሁኔታ መቀጣት፤ በወንጀል እንኳ ሊጠየቁ አይገባም” በማለት በመንግሰታቱ ድርጅት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ራፖርተር ፍራንክ ላ ሩ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሰት በሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ እና በቅርቡም በኤልያስ ክፍሌ፡ዉብሸት ታዮና ርእዮት አለሙ እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅት አባልና ደጋፊ በሆኑ ሁለት ተቃዋሚዎች ላይ የሰጠዉ ፍርድ፤ በሌላ በኩል አንዱአለም አራጌና እስክንድር ነጋን ጨምሮ በሀያ አራት ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተሰጠዉ የጥፋተኝነት ዉሳኔ አሳሳቢ መሆኑን ባለሙያዎቹ አመልክተዋል።
“ በአለም አቀፍ ደረጃ የተረጋገጠዉን የሰዉ ልጆች መብት በማይፃረር መንገድ የፀረ ሽብር ህጉ አላግባብ መጠቀሚያ እንዳይሆን ከአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንፃር በግልፅ መተርጎም ይኖርበታል” በማለት ቤን ኢመርሰን የፀረ ሽብርና የሰብኣዊ መብቶች ልዩ ራፖርተር አሳስበዋል።
አመለካከታቸዉ ከመንግሰት በመለየቱ ምክንያት ብቻ ጋዜጠኞች፤ አስተያየት ሰጪዎችና ሌሎች ለሰብኣዊ መብት መከበር የቆሙ ተሟጋቾች ጫና ሊደረግባቸዉ አይገባም “ በማለት የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ልዩ ራፖርተር ማርጋሬት ሴካ-ጊያ ገልፀዋል።
በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብት እንዲከበር ሃሳቡን በግልፅ ሲያራምድ የነበረዉ ጋዜጠኛና የሰብኣዊ መብት ተሟጋች የሆነዉ የእስክንድር ነጋ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸዉ ልዩ ራፖርተሯ ገልፀዋል።
በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት ልዩ ራፖርተር ሜይና ኪያይ እንዲሁም የዳኞችና የጠበቆች ነፃነት ልዩ ራፖርተር ገብርኤላ ናኡል በየበኩላቸዉ በኢትዮጵያ ፀረ ሽብር ህጉን በመሳሪያነት በመጠቀም መንግሰት በዜጎች ላይ የሚፈፅማቸዉ ድርጊቶች ተገቢ እንዳልሆኑ በመግለፅ የተከሳሾቹ መብት ሚዛናዊ በሆነ የፍርድ ሂደት እንዳልታዬ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሰት የግለሰቦቹን መሰረታዊ መብቶች፤ በተለይም ትክክለኛ ፍትህ ሊያገኙ የሚችሉበት የፍርድ ሂደት መብት አለመታየቱ የፀረ ሽብር ህጉ አገሪቱ የፈረመቻቸዉን አለምአቀፍ የሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎች የተመረኮዘ መሆን አንዳለበት ባለሙያዎቹ ጥሪ ማቅረባቸዉን የመንግስታቱ ድርጅት የዜና ማእከል አስታዉቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስር ላይ የሚገኙት ስዊዲናዊ ጋዜጠኞች ማርቲን ሽብየና ጆን ፒርሰን ዬይቅርታ ደብዳቤ ለአቶ መለስ ዜናዊ ማስገባታቸው ታውቋል።
ጋዜጠኞቹ በኢትዮጵያ የፍርድ ቤት ሂደት ተከራክሮ ማሸነፍ አይቻልም በሚል አመለካከት፣ ይግባኝ ለመጠየቅ የነበራቸውን ፍላጎት ሰርዘው ጉዳዩን በይቅርታ ለመጨረስ ወስነዋል።
ከአለማቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ሲፒጄ፣ ከሂውማን ራይተስ ወችና ከሌሎችም ታዋቂ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው የኢትዮጵያ የሽብርተኝነት አዋጅ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱትን የፖለቲካ ተቃውሞ ለማፈኛነት እየወለነ የሚል ተደጋጋሚ ትችት ቀርቦበታል።
አቶ መለስ እስካሁን ድረስ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርብባቸውን ግፊት ወደ ጎን በመተው፣ ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ ድርጅቶችም በጸረ ሽብርተኝነት ስም ማሰራቸውን ቀጥለዋል።
የአረቡ አለም አብዮት ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ ከ400 በላይ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች መታሰራቸው ይታወቃል።
የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረው ውብሸት ታየ እና የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ እና መምህር የሆነችው ርእዮት አለሙ በተመሳሳይ ክስ በ14 እና በ13 አመታት እንዲሁም የኢትዮጵያን ሪቪው ድረገጽ ዋና አዘጋጅ የሆነው ኤልያስ ክፍሌ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ እንደተወሰነባቸው ይታወሳል።