ብኢኮ ለሙስና የተጋለጠ ድርጅት መሆኑን የጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ

ጥር ፳፮ (ሃያ ስድት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጀኔራል ክንፈ ዳኛው ስራ አስኪያጅነት የሚመራው በስሩ ከ13 በላይ ኩባንያዎችን ዬያዘውና በብዙ ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወይም ብኢኮ አሰራር ግለጽነት የጎደለው መሆኑን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ባወጣው የ6 ወራት ሪፖርት ገልጿል።

ብኢኮ ከተቋቋመበት ከ1995 ዓም ጀምሮ አሰራሩ ለሙስና በር የሚከፍት መሆኑ በተደጋጋሚ በኢሳት ሲዘገብ ቆይቷል። በጥቂት የህወሃት ጄኔራሎች በሚመራው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስም እቃዎች ያለቀረጥ እንዲገቡ እየተደረገ የተወሰኑ ወታደራዊ አዛዦች ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ሃብት እንዲያፈሩና በአዲስ አበባ በተለይም በቦሌ ክፍለከተማ ለገነቡዋቸው ዘመናዊ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች የገንዘብ ምንጭ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከ10 አመታት በሁዋል ጸረ ሙስና ኮሚሽን ብኢኮን በማስመልከት ባወጣው የ6 ወራት የግምገማ ሪፖርት የድርጅቱ አሰራር ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን በዝርዝር አቅርቧል። ኮርፖሬሽኑ በማን እንደሚመራና ይህን የሚመራው አካል እንዴት እንደተቋቋመ እንዲሁም ተጠያቂነቱ ለማን እንደሆነ በግልጽ እንደማይታወቅ የገለጸው ጸረ ሙስና እቃዎች ከተወሰኑ ተቋራጮች ብቻ ስለሚገዙ ግልጽነት የጎደለው ከመሆኑም ባሻገር፣ እቃዎች በምን መስፈረት ከእነዚህ ድርጅቶች ብቻ እንደሚገዙ ፣ የጥራት ደረጃቸውና የአያያዛቸው ስርአት ሁሉ ለሙስና በር የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል።

የኮርፖሬሽኑን ስራ ለመስራት ውል የሚፈጽሙ የስራ ተቋራጮች የሚመረጡበት መስፈርት በተወሰኑ አመራሮች እጅ መውደቁ እንዲሁም የማማከር ስራውንም የሚሰሩት ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ የሚመረጡ በመሆኑ ከአገሪቱ የገበያ ዋጋ ጋር ይጣጣም አይጣጣም እንደማይታወቅ ገልጿል።

በጸረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርት መሰረት ኮርፖሬሽኑ ሀብቱንና የውስጥ አሰራሩን የሚቆጣጠርበት ስርአት የለውም። ምንም እንኳ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ይህን ተከትሎ በኮርፖሬሽኑ ላይ ምርመራ እንደሚጀመር ግልጽ ባያደርግም፣ የማይደፈረውን የመከላከያ ንብረት  ፈራ ተባ እያለም ቢሆን ችግር አለበት ብሎ መጠቆሙ አንድ እርምጃ ነው ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል። የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በአባይ ግድብ ግንባታም  ከፍተኛው ተቋራጭ በመሆን እየሰራ ነው።

ብኢኮ ጋፋት አርማመንት እንዱስትሪ፣ ህበረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ፣ ሆሚቾ አሙኒሽን እንዳስትሪ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ሎኮሞቲቭ፣ ደጀን አቪየሽን እንዱስትሪ፣ አዳማ የእርሻ መሳሪያዎች እንዱስትሪ፣ ብረታብረት ፋብሪኬሽን እንድሱትሪ፣ አቃቂ ቤዚክ ሜታል እንዱስትሪ፣ ኢትዮጵያ ፕላስቲክ እንዱስትሪ፣ አዳማ ጋርመንት እንዱስትሪ እና ሃይቴክ እንዱስትሪ የተባሉ ኩባንያዎችን በስሩ ይዟል።