ባለፉት ሶስት ኣመታት በሠፈራ ፕሮግራም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሕዝብ በአራት ክልሎች እንዲሰባሰብ መደረጉን ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡

ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ2003-2005 ዓ.ም መንግስት መንደር ማሰባሰብ በሚል በሚጠራው የሠፈራ ፕሮግራም በጋምቤላ በ12 ወረዳዎች 38 ሺ፣በቤንሻንጉል ጉሙዝ በ18 ወረዳዎች 77 ሺ ፣በአፋር በ8 ወረዳዎች 10ሺ፣ በሶማሌ በ21 ወረዳዎች 150 ሺ አባወራና እማወራዎች በድምሩ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሕዝብ እንዲሰፍር ተደርጓል፡፡ እስከ2007 የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ ድረስ 85ሺ ቤተሰብ ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው ተብሎአል፡፡ በመንደሩ ያልተሰባሰቡ ሰዎችን በቀጣይ በተሰባሰቡት መካከል የመሰግሰግ ስራ እንደሚከናወን በሪፖርቱ ሰፍሯል፡፡

በአራቱ ክልሎች ለተሰባሰቡ ቤተሰቦች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣የጤና ትምህርት፣የወፍጮ፣ የግብርና መሬትና ግብዓቶች የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሪፖርቱ የጠቀሰ ሲሆን ሌሎች ምንጮች ግን ሰፋሪዎቹ ከአካባቢያቸው ሲነሱ የተገባላቸው ቃል ሙሉ በሙሉ ባለመፈጸሙ መቸገራቸውን፣ አንዳንድ ቦታዎችም ወደቀዩአቸው ለመመለስ በመፈለጋቸው ምክንያት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል፡፡

ሰፋሪዎቹ ካልተሟሉላቸው መሰረተ ልማቶች አንዱ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሲሆን በተለይ በአርብቶአደር አካባቢዎች ሰዎች የለመዱትን የአኑዋኑዋር ዘይቤ ለውጠው ገበሬ እንዲሆኑ የሚደረገውን የካድሬዎች ቅስቀሳን የተቃወሙ ወገኖች እንደተቃዋሚና ጸረሰላም ሃይል በማየት የማስፈራራት ሰለባ ሆነዋል፡፡

አንዳንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች በተለይ አርብቶአደሩ ከከብት እርባታ ስራው ተላቅቆ ወደግብርና እንዲመለስ በመንግስት በኩል የተያዘውን ዕቅድ አይቀበሉትም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰፈራው የህዝቡን ባህል፣ወግ፣ልማድ የሚያሳድግ እንጂ የሚሽር መሆኑ ጉዳት አለው በሚል ምክንያት ነው፡፡ ሆኖም ሪፖርቱ እንደነዚህ ዓይነት ድርጅቶችን የውጪ አክራሪ ኒዮ ሊበራል እና የጸረ ሰላም ኃይሎች ተላላኪዎች እንደሆኑ በማስመሰል ይወነጅላል።