በ97 ምርጫ የካርተር ማእከል የምርጫ ታዛቢ ዋና አማካሪ የኢትዮጵአን ምርጫ ሂደት አጣጣሉት

ሚያዝያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ቴሬንሴ ሊዮንስ በዋሽንግተን ፖስት ላይ “ነጻና ፍትሀዊ ምርጫን ከኢትዮጵያ ጋር ምን አገናኘው?”በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሁፍ በመጪው ግንቦት 16 በ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ የመርሀግብር ማሟያ እንጂ ትርጉም ያለው እንዳልኾነ ገልጸዋል።
ሂደቱ ከቅድመ-ምርጫ ጀምሮ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ እንዳልነበር በስፋት ያብራሩት ጸሃፊው ”ዜጎች አዲስ መንግስት የማይመርጡበት ትርጉም የለሽ ምርጫ”ሲል አጣጥለውታል።
የአሜሪካ ምክትል የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ወንዲ ሸርማን ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ሀገር ማለታቸውና በመጪው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውንም ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ ብለው ማሞካሸታቸውን ተችተዋል።
ጸሃፊው እንደሚሉት ምርጫው ለውጭ አገር ህጋዊ ተቀባይነት ማስገኛ ተብሎ በየጊዜው ከሚደረግ ይልቅ፣ በአገር ውስጥ ያለውን ህዝብ ለመቆጣጠርና አፈና ጉልበትን ለማሳየት ተብሎ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጆርጅ ማሶን ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፀጻፊው ፣ ገዢው ፓርቲ በ2002 ምርጫ ካገኘው ውጤት ያልተናነሰ እንደሚያገኝም ገልጸዋል።