በፕሬዝዳንት ሙላቱ ፊርማ የተፈቱት አቶ ከበደ ተሰራ እንደገና ታሰሩ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 12/2006)ወርልድ ባንክ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት አቶ ከበደ ተሰራ በፕሬዝዳንቱ ይቅርታ ከተደረገላቸው 92 ታሳሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ከእስር የወጡት ሰኔ 24 2009 ነበር።

ከ13 ቀናት ከእስር ቤት ውጭ ቆይታ በኋላም በድጋሚ በጸጥታ ሃይሎች ታጅበው ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል።

የፕሬዝዳንቱን የይቅርታ ፊርማ በመሰረዝ ወደ ዘብጥያ እንዲመለሱ የተደረገው ከስምንት አመታት በፊት ተከሰው ከተፈረደባቸው የ25 አመታት የእስር ቅጣት ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በአራጣ ማበደር፣በታክስ መሰወር፣ሐሰተኛ ሰነድ በማቅረብና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ሲያካሂዱ የሚያሳይ ማስረጃ በማቅረቡ ነበር አቶ ከበደ ተሰራ ለ25 አመታት እስርና ለ 300 መቶ ሺ ብር ቅጣት የተዳርጉት።

አቶ ከበደ ከ25 አመታቱ የእስር ፍርድ ያጠናቀቁት 8 አመት ከ2 ወሩን ብቻ ነው።ይህ ደግሞ በይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ስነስርአት ከተፈረደባቸው 25 አመት ግማሹን መፈጸም አለባቸው።–እሳቸው ደግሞ ይህንን መፈጸም ባለመቻላቸው ወደ እስር ቤት እንዲመልሱ ተደርጓል ነው ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ በእትሙ።

በአዋጅ ቁጥር 840/2006 ተጠሪነቱ ለፕሬዝዳንቱ የሆነው የይቅርታ ጥያቄዎችን የሚመረምርውና ለፕሬዝዳንቱ የሚያቀርበው ቦርድ ጉዳያቸውን ከተመልከተው 92 ታሳሪዎች መካከል አንዱ ከበደ ተሰራ ነበሩ።

ቦርዱ ታዲያ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት አቶ ከበደ ከሌሎች ይቅርታ ጠያቂዎች ጋር የፕሬዝዳንቱን የይቅርታ ፊርማ እንዲያገኙ አድርጓል።

ሐምሌ 7 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ከበደ ወደ ማረሚያ ቤት ተመልሰው በእስር ላይ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል።

ቦርዱ አቶ ከበደ ከሌሎች ይቅርታ ጠያቂዎች ጋር እንዴት ሊቀላቀሉ ቻሉ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ያለው ነገር የለም።

በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የተሰጠ የይቅርታ  ፊርማ መሰረዝ ይችላል ወይ የሚለው ደግሞ የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል።