ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል በመንገድ ግንባታ ሥም ሊፈርስ ነው

ሐምሌ ፲፫ ( አሥራ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ቅርስና ኪነጥበብን ለማስተዋወቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በግል ተነሳሽነት የተቋቋመው ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል በመንገድ ግንባታ ሥም የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል። በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኘውና በአንድ ግቢ ውስጥ የነገስታትን ታሪክ፣ የታሪካዊ ቦታዎችን፣ ባህላዊ እሴቶችን እና ዕደጥበቦችን በምስል አስደግፎ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ በመሆን የአገር ባለውለታ ተቋም ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደርና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም በማዕከሉ በር ላይ እንዲፈርስ የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያ ለጥፏል። መስተዳድሩ በማስታወቂያም የቤቱን ልኬት ለመውሰድ በተደረገ ጥረት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የልማት እንቅፋት መሆናቸውን ከመግለፁም ባለፈ ይህ ደብዳቤ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ የስራ ቀናት ወደ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽ/ቤት ቀርበው ሪፖርት ካላደረጉ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቋል።
ውሳኔውን ተከትሎ የማእከሉ መስራች ዋና ስራስኪያጅ እና ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ ሳቤላ በላይነሽ አባይ የማእከሉን አደጋ ውስጥ መውደቅ አስመልክቶ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። “ይህ ቤት ኢትዮጵያን ለአገር ውስጥና ለውጪ ጎብኚዎች የሚያስተዋውቅ ማዕከል እንጂ እንደማንኛውም የግለሰብ መኖሪያ ቤት ይፍረስ ተብሎ የሚገለፅ አይደለም። እኔም የአገሪቱን ልማት የማደናቀፍ ተደርጎ መተርጎም የለበትም” ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን የተሰማቸውን ቅሬታ ገልፀዋል። ይህን የአገር ባለውለታ ድርጅት ለመታደግ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች እና አገር ወዳድ ዜጎች የተቻላቸውን እንዲያደርጉም ተማጽነዋል።
የመፍረስ ስጋት ያጋጠመው ይህ “ትንሿ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ማዕከል ለመንገድ ስራ በሚል የሚያጣው የ5 ሜትር ስፋቱ ማዕከሉ ሊያመለክታቸው የቆማቸውን የድሬዳዋ፣ የሀረር፣ የአክስምና የጎንደር ምልክት የሆኑ ጥበባዊ ስራዎችም አብረው የሚፈርስበት በመሆኑ ከዚያ በኋላ እንደ ማዕከል የመቀጠሉ ነገር የማይታሰብ መሆኑንም ወ/ሮ ሳቤላ በላይነሽ አባይ በአፅንኦት ተናግረዋል። ብርሃን ኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ መመስረቱንም ሰንደቅ ጋዜጣ አክሎ ዘግቧል።