በፓርላማ አባላት ላይ የሚደረገው ማስፈራሪያ ተጠናክሮ ቀጥሏል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21 2010)

የአስቸኳይ ገዜ አዋጁን እንዲያጸድቁ በፓርላማ አባላት ላይ የሚደረገው ማስፈራሪያ ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቀ።

ፋይል

ከኦህዴድ አባላት በተጨማሪ በብአዴን እና ደኢህዴን አባላት ላይ ጭምር በተጠናከረው በዚሁ የማስፈራራት ርምጃ በዋናነት የሚሳተፉት ከመከላከያ ሚኒስቴር የተላኩ ጄኔራሎች እና የደህንነት  ሰራተኞች መሆናቸውን ለኢሳት የደረሰው መራጃ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ደኢህዴን በአቶ ሃይለማርያም ምትክ ሊቀመንበር የመረጠውና በኋላም የቀየረው በሕወሃት መሪዎች ትዕዛዝ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የካቲት 9 /2010 በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ፣በፓርላማው እንዲጸድቅ መርሃ ግብር የተያዘለት ለፊታችን አርብ የካቲት 23/2010 ሲሆን፣ይህ ዕልቂት ያነግሳል ተብሎ የተሰጋው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንዳይጽድቅ ለፓርላማ አባላቱ ጥሪ በመደረግ ላይ ይገኛል።

የኦህዴድ አመራር የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንዳይታወጅ ሲያራምድ በቆየው አቋም ሳቢያ የኦሮሚያ ክልል የፓርላማ ተመራጮች አዋጁን ይቃወማሉ ተብሎም ተጠብቋል።

የኦሮሞ አክቲቪስቶችም የፓርላማ አባላቱን ስልክ በማሰራጨት ሕዝቡ ግፊት እንዲያደርግባቸው ተንቀሳቅሰዋል።

የአክቲቪስቶቹ እንቅስቃሴ የፓርላማ አባላቱ አዋጁን ባለማጽደቅ ወገኖቻቸውን እንዲታደጉ ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሃገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት እና የመከላከያ ሚኒስቴር በቅንጅት የፓርላማ አባላቱ አዋጁን እንዲያጸድቁ የተጠናከረ ዘመቻ ተጀመሯል።

የፓርላማ አባላቱ አዋጁን እንዲያጸድቁ ማስገደድ ብቻ ሳይሆን ፣በማናቸውም ሁኔታ ከፓርላማ መቅረት እንደማይችሉ ማሳሳቢያ በመሰጠት ላይ ይገኛል።

ማስፈራሪያው በኦህዴድ ላይ አባላት ላይ የተወሰነ ሳይሆን፣ የብአዴን እና የደኢህዴን አባላትን የጨመረ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

የፓርላማ አባላቱን ለማስፈራራት የመከላከያ ሚኒስቴር ጄኔራሎች ተሳታፊ ሆነዋል። አዋጁ ባይጸድቅና ችግር ቢፈጠር ተጠያቂ ናችሁ በማለትም የፓርላማ አባላቱን አስፈራርተዋል።

ፓርላማውን እስከመበተን የዘለቀ ርምጃ እንደሚወሰድም ዝተዋል።

የፊታችን አርብ የሚሰበሰበው ፓርላማ አዋጁን በ2/3ኛ ድምጽ ካላጻደቀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ህጋዊነት ያበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ሲራጅ ፈጌሳን የደኢህዴን ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠውና በኋላም አቶ ሽፈራው ሽጉጤን እንደገና የመረጠው በህወሃት መሪዎች ትዕዛዝ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በሁኔታው የተበሳጩ የደኢህዴን ማዕከላዊ አባል እንደ ኦህዴድ የፈለግነውን የምንመርጠው መቼ ነው? በማለት በስብሰባው ላይ መጠየቃቸውም ተመልክቷል።

ሲራጅን ምረጡ ብለው አስገደዱን ፣ሲራጅን መረጥን ፣አሁን ደግሞ ሲራጅን ምክትል አድርጉት እና በግምገማ በማስጠንቀቂያ የታለፈውን ሽፈራው ሽጉጤን ምረጡ አሉን።

አሁንስ ተናጋሪ እቃ አደርጉን እኮ! እኛ መቼ ነው እንደ ኦህዴድ በነጻነት የፈለግነውን የምንመርጠው? አሁንስ ኦህዴድ መሆን አማረኝ ሲሉ የድጋፍ ጭብጨባ እንዳጀባቸውም የደኢህዴን ምንጮች ገልጸዋል።