ህወሃት የዶ/ር አብይ አህመድን መመረጥ አጥብቆ እየተቃወመ ነው

ህወሃት የዶ/ር አብይ አህመድን መመረጥ አጥብቆ እየተቃወመ ነው
(ኢሳት ዜና የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ለመተካት ኦህዴድ በእጩነት ለማቅረብ ያዘጋጃቸው ዶ/ር አብይ እንዳይመረጡ፣ ህወሃት ጠንካራ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ነው። የደረሱን ተጨባጭ መረጃዎች እንደሚያመለክቲት፣ህወሃቶች ዶ/ር አብይን “ትግሬን ይጠላል” የሚል ቅስቀሳ ከፍተውባቸዋል።
የኦሮምያ ክልል መሪ አቶ ለማ መገርሳ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ዶ/ር አብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲሰሩ የተደረገው ለስልት ነው በማለት ተናግረው ነበር፡፡ “ ለፌዴራል የሚሄድ አካል እንዴት መስራት እንዳለበት፤ ምን መስራት እንዳለበት ግንዛቤ በመያዝ ይሄን ማስተካከያ አድርገናል፡፡ ሁለቱም አካላት ደግሞ በመደማመጥ ፤ በመተጋገዝ ይሰራሉ ብሎ ድርጅቱ አምኖበት ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀጣዩን ስራ በማጤን ወስኗል፡፡” በማለት ዶ/ር አብይ በፌደራል ደረጃ እንዲሰሩ መታጨታቸውን በተዘዋዋሪ መልኩ ገልጸው ነበር። የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክም ዶ/ር አብይን በተመለከተ ባቀረበው አንድ ዝግጅት ኦህዴድ ዶክተሩን በእጩነት ለማቅረብ መወሰኑን አመላክቷል።
ይህንን ተከትሎ በአቶ በረከት ስምዖን ስም የወጣ እና በህወሃት አባሎች የተሰራጨ ዶ/ር አብይን የሚተች አንድ ጽሁፍ በማህበራዊ ሚዲያ ተለቋል። አቶ በረከትም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ጽሁፉ የእርሳቸው እንዳልሆነ አስተባብለዋል። ይሁን እንጅ ህወሃቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በዶ/ር አብይ ላይ ጠንካራ ዘመቻ በመክፈት ዶ/ሩ እንዳይመረጡ ቅስቀሳ ጀምረዋል።
ህወሃቶች “ ዶ/ር አብይ ስር የሰደደ የትግሬ ጥላቻ አለበት” የሚል ቅስቀሳ የጀመሩ ሲሆን፣ ዶክተሩን የሚያጠለሹ የተለያዩ መረጃዎችንም በመልቀቅ ላይ ናቸው። በተለይም ኢንሳ እየተባለ በሚጠራው ተቋም ውስጥ ሲሰሩ በነበረበት ወቅት ዶ/ር አብይ ፣ የኢንሳን ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተክለብርሃንን ከሰራተኞች ለመነጠል ሙከራ ማድረጋቸውን፣ የመከላከያ ቦታውን ትተው ወደ ሲቪል ስልጣን ከመጡ በሁዋላም በትግራይ ተወላጆች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ጥላቻቸውን” አሳይተዋል የሚል ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ናቸው።
ህወሃት አሁን ያለው የአቶ ለማ መገርሳና የዶ/ር አብይ ቡድን ወደ ማእከላዊ ስልጣን መምጣቱን አጥብቆ ቢቃወምም፣ ኦህዴድ ያቀረበው እጩ የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ ካልያዘ በኦሮምያ ክልል ሰላም አይወርድም የሚል ስጋት አድሮበታል።
በቅርቡ የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ በሚያደርገው ስብሰባ አዲስ የጠ/ሚኒስትር ምርጫ ይካሄዳል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ህወሃቶች ከአገሪቱ ችግር ይልቅ የራሳቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ እየሰሩ ነው በማለት ተቃውሟቸውን መግለጽ የጀመሩ ቢሆንም፣ በምርጫው ውጤት ላይ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ እንደማይፈጥሩ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።
በሌላ ዜና ደግሞ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት በኮማንድ ፖስቱ አንድ በአንድ መታሰር ጀምረዋል። የኦሮምያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ ስልጣን የለቀቁ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ሰሞኑን ተቃውሞ ሲካሄድባት የነበረው የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ ካባ ሁንዴ ከቄሮ ጋር ግንኙነት ፈጥረሃል በሚል በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ካባ ቀደም ብሎ የቄለም ወለጋ ግብርና ሃላፊ ሆነው ሲሰሩ ከቆዩ በሁዋላ ነው ከአመት በፊት የከተማው ከንቲባ ሆነው የተሾሙት። አቶ ካባ መከላከያው ከከተማው እንዲወጣና የክልሉ ፖሊስ ብቻ ጥበቃ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበው ነበር።ይሁንና የኮማንድ ፖስቱ አባላት ከንቲባውን ይዘው ወደ አልታወቀ ስፍራ ወስደዋቸዋል።