በፍርድ ቤት ውሳኔ የተፈቱት ሰላማዊ ዜጎች በድጋሚ በመንግስት ታፈኑ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 17, 2007)

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኞ ከእስር እንዲፈቱ የወሰነላቸው አራት የፓርቲ አባላት ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች በድጋሚ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አራቱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ከተከሳሾች ፍርድ ቤት ካስተላለፋቸው ከሁለት ወር በላይ በእስር ቤት በመቆየታቸው ምክኒያት ሰኞ ከእስር እንዲፈቱ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

አራቱ ተከሳሾች ማክሰኞ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲወጡ ቢደረግም በእስር ቤቱ በር ላይ ፖሊሶች እና የደህንነት ሀይሎች ከእስር የተፈቱትን አባላት በድጋሚ ለእስር እንደዳረጉዋቸው ከሀገር ቤት የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በቂሊንጦ እና ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የነበሩት ተከሳሾች መንግስት በሊቢያ የተገደሉ ኢትዮጲያንን ግድያ ለማውገዝ ጠርቶ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ብጥብጥ ለማስነሳት ተንቀሳቅሰዋል በሚል ለእስር ተዳርገው መከሰሳቸው ይታወሳል።

ጉዳያቸውን ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤትም ትላንት ሰኞ ባስተላለፈው ውሳኔ ተከሳሾች ከተላለፈባቸው የሁለት ወር የእስር ቅጣት በላይ በእስር ቤት በመቆየታቸው ከእስር እንዲፈቱ ወስኗል።

ይሁንና የቂሊንጦ እና 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ኤርሚያስ ጸጋዬ፤ ዳንኤል ተስፋዬ ፤ ወይንሽት ሞላንና ቤተልሄም አካለወርቅ ከእስር ቤት ቢፈቷቸውም የጸጥታ ሀይሎች በደቂቃዎች ልዩነት በድጋሚ በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።

አራቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በነጻ እንዲሰናበቱ ከተወሰነ በኋላ በምን ምክኒያት በድጋሚ ለእስር እንደተዳረጉ ከመንግስት አካላት የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ከሀገር ቤት የደረሰን መረጃ አክሎ አመልክቷል ።

ከወረት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ መንግስት በሊቢያ የተገደሉ ኢትዮጵያዊያንን ግድያ ለማውገዝ ጠርቶ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ብጥብጥን ለማስነሳት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ከ 1ሺ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ለእስር ከተዳረጉ መካከልም ከመቶ የሚበልጡ ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኝ ሲሆን አራቱ የፓርቲ አባላት ከእስር እንዲፈቱ ውሳኔ ሲተላልፍ የመጀመሪያው እንደሆነ ታውቋል።
የቀሪ ታሳሪዎች የክስ ሂደትም በተላያዩ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በመካሄድ ላይ ይገኛል።