የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ የጉብኝት በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቃውሞ አስነሳ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 17 2007)

በቀጣዩ ወር በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ተቃውሞ እንደገጠማቸው የእንግሊዙ ዘጋርዲያ ጋዜጣ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ዛሬ ረቡእ ዘገበ።

አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ፕሬዚዳንቱ በሰብአዊ መብት ረገጣና አፈና የምትታወቅ ሃገርን ለመጎብኘት መወሰናቸው ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ መሆናቸውንም ጋዜጣው አስነብቧል።

የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስደንጋጭ ዜና ሆኗል ያለው የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ተቋማቱ የኦባማ ጉብኝት ጨቋኝ ለሆነው የኢትዮጵያ መንግስት የተሳሳተ መልእክት ሊያስተላልፍ እንደሚችል ስጋት እንዳደረባቸው አመልክቷል።

የአሜሪካ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬዚዳንቱ የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት በቀጠናው ስላለው የኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የዲሞክራሲ ተቋማትና የደህንነት ሁኔታዎች እንዴት መጠናከር እንዳለበት ያለመ መሆኑን ገልጿል።

ይሁንና ፕሬዚዳንቱ በሰብአዊ  መብት ረገጣዋ የቆየ ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያ መጎብኘታቸው ተገቢ አለመሆኑን በርካታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ከእንግሊዙ ጋዜጣ በተጨማሪ ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ዘግበዋል።

የሂዉማን ራይትስ ዎች ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ኬኔት ሮስ አሜሪካ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማካሄዱዋ ተገቢ አለመሆኑን እና በተዘዋዋሪ እውቅና የመስጠት ድርጊት ተደርጎ እንደሚታይ ገልጸዋል።

ፍሪደም ሃውስ የተሰኘ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጀት በበኩሉ ኢትዮጵያ ሁሉንም የተቃዋሚ ድርጅቶች ከፖለቲካ ተሳትፎ ዉጭ አድርጋ ባለበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ በሃገሪቱ ጉብኝት ማድረጋቸው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ረፖርትን ያወጣው ግሎባል ቮይስ የተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሊጎበኟቸው ካቀዷቸው ሃገራት መካከል የኢትዮጵያው ጉብኝት ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱን ገልጸዋል።

ተቃውሟቸውን በማቅረብ ላይ የሚገኙት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ፕሬዚዳንቱ ከጉብኝታቸው እንዲታቀቡ ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውንም ግሎባል ቮይስ በሪፖርቱ አመልክቷል።

በቀጣዩ ወር የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ጉብኝታቸውን የሚያድርጉት ኦባማ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአፍሪካ ህብረት እና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።