ታህሳስ 16 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ተማሪዎች እርምጃ የተወሰደባቸው በግቢው ውስጥ ተከስቶ የነበረውን በሽታ ምክንያት በማድረግ ረብሻ አስነስተዋል ተብሎ ነው።
ከ50 ተማሪዎች ውስጥ 22ቱ በአንደኛ ደረጃ ጥፋተኝነት ተፈርጀው ለአንድ ዓመት ከትምህርታቸው እንዲገለሉ ሲደረግ ፣ 18ቱ ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ተማሪዎች ላወደሙት ንብረት ተጠያቂ እንደሆኑና እንዲከፍሉ ታዘዋል።
ገንዘቡን ካልከፈሉ የትምህርት ማስረጃቸው የማይሰጣቸው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላም በማንኛውም ዓይነት ጥፋት ውስጥ ቢሳተፉ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲው ይባረራሉ በማለት የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር ተናግረዋል።
‹‹ዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ ዩኒቨርሲቲ ነው›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መልካም ስሙን ላለማጣት ሲል ብዙ ጊዜ ዕርምጃ አይወስድም፡፡ አሁን ግን ተማሪዎቹ በዚህ መልኩ ካልተማሩ በቀጣዩ ሥርዓተ አልበኝነት ስለሚከሰት ቅጣት ማስተላለፉ ግድ ሆኗል ብለዋል፡፡”
ቅጣቱ ከተላለፈባቸውም መካከል ተመራቂና ሴት ተማሪዎች ይገኙበታል።
በጐንደር ዩኒቨርሲቲ ማራኪና ቴዎድሮስ ግቢዎች ውስጥ ከአንድ ወር በፊት ‹‹ሽጌላ›› በተባለ ከተበከለ ምግብ ወይም ውኃ በሚነሳ ባክቴሪያ ሳቢያ በተቀሰቀሰ ወረርሽኝ ከ1 ሺ በላይ ተማሪዎች መታመማቸው ይታወቃል።
መንግስት ተማሪዎቹ በተበከለ ምግብ በመታመማቸው ሀላፊነቱን ሳይወስድ ፣ የመንግስትን ድርጊት በተቃወሙ ተማሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ነገሩን እንቆቅልሽ አድርጎታል።