ህዳር 19 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከሆስፒታል ምንጮች የደረሰን ዘገባ እንደሚያሳየው የምግብ መመረዙ የተከሰተው ማራኪና ቴዎድሮስ በሚባሉ ሁለት የዩኒቨርስቲው ካምፓሶች ውስጥ ነው።
በአንደኛው ግቢ ውስጥ የሆስፒታል አልጋዎች በመጣበባቸው ተማሪዎች በዬመኝታ ክፍላቸው ተኝተው እንዲታከሙ ተደርጓል። መንግስት መረጃው ወደ ውጭ እንዳይወጣ ለሀኪሞቹ ትእዛዝ መሰጠቱንም ለማወቅ ተችሎአል።
ከዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሰራተኞች እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ችግሩ የተፈጠረው የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ ለተማሪዎች የሚቀርበው ምግብ ጥራት የጎደለው መሆኑ ነው።
ተማሪዎች የሚቀርብላቸው ምግብ ጥራት የሌለውና በምግብ ይዘቱም ደካማ ተማሪዎችን ለምግብ መመረዝ የሚዳርግ መሆኑን የአስተዳደር ሰራተኞቹ ተናግረዋል።
በተማሪዎች ላይ የደረሰውን የምግብ መመረዝ ተከትሎ የተወሰኑ ተማሪዎች ተቃውሞ ለማስነሳት ቢሞክሩም፣ ተቃውሞአቸው በፌደራል ፖሊሶች እንዲታፈን ተደርጓል።
አሁንም ግን በሁለቱም ግቢዎች ትምህርት አለመጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎንደር ከተማ የውሀ እና የመብራት እጥረት መከሰቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
መብራት እና ውሀ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖብናል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ።