(ኢሳት ዜና–መስከረም 15/2010)በግጨው ጉዳይ ብአዴን ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሜቴና የአማራ ክልል ካቢኔ በማያውቁት ሁኔታ ግጨውን ለትግራይ ክልል አሳልፈው መስጠታቸው በባህርዳር እየተካሄደ ባለው አጠቃላይ የድርጅት ጉባዔ ላይ ዋና አጀንዳ ሆኖ መነሳቱ ታውቋል።
ባለፈው ሳምንት ያለስምምነት የተበተነውን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባን ተከትሎ የተጠራው የድርጅቱ አጠቃላይ ጉባዔ የህወሀት የበላይነትን በግንባር ቀደምትነት በማንሳት ውይይት አካሂዷል።
በውጥረት የታጀበው ይህው ስብሰባ ለሁለት ተከፍሎ እየተካሄደ ሲሆን የሞባይል ስልክ ወደ ስብሰባ አዳራሽ እንዳይገባ መደረጉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የክልል የዞንና የወረዳ ሴክተር መስሪያ ቤት ሃላፊዎች፣ የድርጅት አመራሮች፣ የተሳተፉበት የባህርዳሩ ጉባዔ በብአዴን ውስጥ የተፈጠረውን የሃይል አሰላለፍ ልዩነት ግልጽ አድርጎታል ይላሉ የኢሳት ምንጮች።
ባለፈው ሳምንት ያለስምምነት በተቋጨው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የአቶ ዓለምነው መኮንን ፍጥጫ ጎልቶ መታየቱ የተጠቀሰ ሲሆን አቶ ዓለምነው የቅማንትን ጉዳይ በማንሳት አቶ ገዱን ተጠያቂ አድርገዋል ተብሏል።
ከህወሀት መሪዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸውና በብአዴን ውስጥ የህወሀትን ጥቅም ለማስከበር እንደሚሰሩ የሚታመኑት አቶ ዓለምነው መኮንን አቶ ገዱን ጨምሮ የተወሰኑ አፈንጋጭ ያሏቸውን አመራሮች ለማስወገድ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይነገራል።
ትላንት በባህር ዳር ክልል ምክር ቤት የተጀመረው ጉባዔ ላይ በተለይ ሁለት ጉዳዮች ከፍተኛ ውዝግብ የተፈጠረባቸው ሲሆን ስብሰባውን ለመቀጠል ባለመቻሉ ለሁለት እንዲከፈል መደረጉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ሁለተኛው የተከፈለው ቡድን በስራ አመራር ተቋም አዳራሽ ውስጥ ስብሰባውን መቀጠሉን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ብአዴን ቅርቃር ውስጥ የገባበትና ለህልውናው ከወሳኝ ምዕራፍ የተጠጋበት ሁኔታ መፈጠሩንም ይገልጻሉ።
የበላይ አመራሮች ከመካከለኛውና ከታችኛው የድርጅት አመራሮች ጋር የሚያደርጉት ውይይት ያለስምምነት በተቋጨው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተነሱትን አጀንዳዎች ጨምሮ በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አንገት ለአንገት ተናንቀው በመፋጨት ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የግጨው ጉዳይ አቶ ገዱን ከድርጅትና ካቢኔ አባላት ጋር ፍጥጫ ውስጥ የከተታቸው ሲሆን በፓርቲም ሆነ በክልል መንግስት ደረጃ ያልታወቀውና ስምምነት ያላገኘበትን የግጨውን ጉዳይ በፊርማ ወደ ትግራይ ክልል እንዲጠቃለል የተደረገበትን ውሳኔ በተመለከተ አባላቱ ግልጽ ማብራሪያ እንደሚፈልጉ በጉባዔው ላይ አንስተዋል።
ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የግጨውን ጉዳይ ከድርጅታቸውና ከክልሉ ካቢኔ አባላት ዕውቅና ውጪ በህወሀት አስገዳጅነት ተስማምተው ሰጥተዋል።
በተወሰነ ደረጃ በድርጅታቸው ውስጥ ተቀባይነት የነበራቸው አቶ ገዱ ግጨውን ተስማምተው ካስረከቡ በኋላ ግን ብቻቸውን መቅረታቸው ይነገራል።
ይህን አመቺ አጋጣሚ በመጠቀም አቶ ዓለምነው መኮንን በቅማንት ማህበረሰብ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል በሚል አቶ ገዱን ሊያስወግዱ እንደሚችሉ ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በዚሁ ጉባዔ የህወሀት የበላይነት ቁልፍ አጀንዳ ሆኖ በአባላቱ መነሳቱም ተገልጿል።
ከመድረክ አጀንዳው እንዳይነሳ ጥርት ቢደረግም የተሳታፊዎቹ ቁልፉ ጉዳይ የህወሀት የበላይነት በመሆኑ ልንወያይበት ይገባል ብለው አቋም ይዘዋል።
ባለፈው ሳምንት በተደረገው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ላይ ይህው አጀንዳ ተነስቶ አመራሮች የተከራከሩበት ሲሆን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ዶክተር አምባቸው መኮንን አመለካከታቸው የተስተካከለ ሆኗል በሚል በአቶ ዓለምነው መኮንን ሪፖርት መቅረቡም ታውቋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ አሁንም ህወሀትን እንደጠላት አድርጎ የመፈረጅ አዝማሚያ በአንዳንድ አመራሮች በኩል አሁንም እንዳለ የጠቀሱት አቶ ዓለምነው ይህ አመለካከት በአስቸኳይ መወገድ አለበት ማለታቸው ተገልጿል።
ሆኖም ያለስምምነት የተበተነው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ በህወሀት የበላይነት ጉዳይ ላይም አንድ አቋም መውሰድ እንደተሳነው የተገለጸ ሲሆን ትላንት በተጀመረው አጠቃላይ ጉባዔ ላይ ትልቁ የመወያያ ርዕስ ሆኖ መቅረቡን የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በፍጥጫ የታጀበው የባህርዳሩ ጉባዔ ለ10 ቀናት የሚቆይ እንደሆነም ታውቋል።