በደብረታቦር ወጣቶችና የሀይማኖት አባቶች ታፍሰው መወሰዳቸው ታወቀ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 15/2010)በደብረታቦር ትላንት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ወጣቶችና የሀይማኖት አባቶች ታፍሰው መወሰዳቸው ተገለጸ።

በኢየሱስ ደብር የሚተከለውን የመረጃ ቋት ማማ በመቃወም ወደቤተክርስቲያን መስቀል ይዘው በተመሙ ነዋሪዎች ላይ የመንግስት ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው በርካታ ሰዎች ቆስለዋል።

ደብረታቦር ቁጥሩ የበዛ የመንግስት ሃይል የገባ ሲሆን ቤት ለቤት በመዘዋወር ወጣቶችን አፍሰው ወስደዋል።

ተቃውሞውን አስተባብረዋል በሚልም የተወሰኑ የሃይማኖት አባቶች መታሰራቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የኢየሱስ ደብር ቤተክርስቲያን አባት አባ ብርሃን በድጋሚ ከታሰሩ በኋላም ወዴት እንደተወሰዱ የታወቀ ነገር የለም።

መነሻው በደብረታቦር ኢየሱስ ደብር ቅጥር ግቢ ለመትከል የታቀደውና ግንባታው የተጀመረው የመረጃ ቋት ምሶሶ ነው።

የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች ባልተጠየቁበት፣ ምዕመናን ባልመከሩበት ሁኔታ መንግስት ለክልሉ ቴሌቪዥን አገልግሎት የሚሆን ምሶሶ በቤተክርስቲያኒቱ ግቢ ለመትከል ከውሳኔ ላይ በመድረስ እንቅስቃሴ ይጀምራል።

ሁኔታው ያስቆጣቸው የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች ለምዕመናን ጉዳዩን በማሳወቃቸው ጉዳዩ ለህዝብ ይደርሳል።

ባለፈው ሀምሌ የደብረታቦር ህዝብ ወደ ኢየሱስ ደብር በመትመም ተቃውሞ አሰማ።

በወቅቱ በመንግስት የታሰሩትን የቤተክርስቲያኒቱን አባት አባ ብርሃን እንዲፈቱ አደረገ። የህዝቡ ተቃውሞ ጠንካራ ስለነበረ የምሶሶው ግንባታ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል።

ይሁንና ባለፈው ሳምንት ሀሙስ የምሰሶው ግንባታ መቀጥሉን ተከትሎ ተቃውሞ ሊመጣ ይችላል በሚል አባ ብርሃን በመንግስት ታጣቂዎች ታፍነው ተወሰዱ። የአባ ብርሃን መታሰር እንደተሰማ የደብረታቦር ህዝብ ተቃውሞውን ሊገልጽ ትላንት ዕሁድ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ አመራ።

በቦታ የጠበቀው ግን ብዛት ያለው የመንግስት ታጣቂ ነበር። መስቀል ይዘው የታሰሩት አባት ይፈትሉን የሚል ድምጽ ሲያሰሙ በነበሩ ምዕመናን ላይ ታጣቂዎቹ ተኩስ ከፈቱ። አካባቢው በዋይታ ተሞላ

ትላንት የመንግስት ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች ተጎደተዋል። –ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውም ወደ ህክምና ማዕከላት መወሰዳቸው ታውቋል።

ከተማዋን የወረረው የመንግስት ታጣቂ ሃይል ለተቃውሞ የወጣውን ህዝብ በሰደፍና በቆመጥ ዱላ በመደብደብ እንዲበተን አድርጓል።

ሌሊቱን ወደ ደብረታቦር የገባው ተጨማሪ የመንግስት ሃይል በደብረታቦር ወጣቶች ላይ የአፈሳ ዘመቻ መክፈቱን ዛሬ ከዚያው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የደብረታቦር ወጣቶች የታፈሱ ሲሆን አብዛኞቹን የት እንደወሰዷቸው የታወቀ ነገር የለም።

ከወጣቶቹ በተጨማሪ ከ20 በላይ የሃይማኖት አባቶች መታሰራቸው ታውቋል። አዲስ የተሾሙት የደቡብ ጎንደር ሀገርስብከት ጳጳስ አባ ሃይለማርያም በጉዳዩ ላይ ዝምታን የመረጡ ሲሆን በዚህን ወቅት በአዲግራት የቆመውን ግዙፍ መስቀል ለመመረቅ ከፓትሪያርኩ ጋር መቀሌ መግባታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ ታፍነው የተወሰዱት የኢየሱስ ደብር አባት አባ ብርሃንን ለመጠየቅ ወደ እስር ቤት የሄደው ህዝብ ባለፈው ቅዳሜ ካያቸው ወዲህ የት እንዳደረሷቸው ማወቅ እንዳልቻለ አሁን ዘግይቶ የደረሰን ዜና አመልክቷል።

አባ ብርሃን አሁን ላይ የት እንደታሰሩ ባይታወቅም ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ግን የረሃብ አድማ ላይ እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።