በግብጽ በፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት በተቃዋሚዎችና በፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች መሀከል በተነሳ ግጭት 5 ሰዎች መገደላቸውንና ከ 644 በላይ መቁሰላቸውን ቢቢሲ ዘገበ::

 ህዳር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ይህን ግጭት ተከትሎም የግብጽ ሰራዊት ከፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት አካባቢ ተቃዋሚዎችንና የመገናኛ ብዙሀን አባላትን በማስወጣት ላይ ይገኛል::

ከቤተ መንግስቱ አካባቢ እንዲለቁ በተሰጣቸው የሰአት ገደብ መሰረት አብዛኖቹ ተቃዋሚዎች መልቀቃቸው ሲታወቅ የተወሰኑ የተቃዋሚ አክቲቪስቶች በዛው እንደሚገኙ የቢቢሲዘገባ አመልክቶል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋነኛው የግብጽ እስላማዊ አካል ፕሬዚዳንት ሙርሲ የሀገሪቱን አጠቃላይ ስልጣን እንዲቆጣጠሩ ያስችላቸዋል የተባለውን ህግ እንዲያነሱ ጠይቆል::

የአል አዛሪ ማእከል በበኩሉ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለውይይት እንዲቀመጡ ጠይቆል::

ፕሬዚዳንት ሙርሲ የህግ አካሉን ስልጣን ጭምር እንዲቆጣጠሩ የሚያደርግና እሳቸው የወሰኑትን ውሳኔ የትኛውም የህግ አካል እንዳይቀለብስ  ያስቻላል የተባለ ህግ በኖቬምበር 22 ይፋ ማድረጋቸው ነበር የአሁኑን ተቃውሞ ያስነሳው::

ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ሙስሊም ብራዘር ውድን ወክለው ተቃዋሚዎችን በጠባብ ልዩነት በማሸነፍ ፕሬዚዳንት ለመሆን መብቃታቸው ይታወቃል::