በእስር ላይ በሚገኙት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት እስላማዊ መንግስት ለመመስረት እንሰራ ነበር ብላችሁ እመኑ በመባል እየተደበደቡነ እየተሰቃዩ መሆኑ ተገለጠ

ህዳር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በእስር ላይ በሚገኙት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት እስላማዊ መንግስት ለመመስረት እንሰራ ነበር ብላችሁ እመኑ በመባል እየተደበደቡነ እየተሰቃዩ  መሆኑ ተገለጠ::

በዛሬው እለት የነበራቸው ቀጠሮም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መሰረዙ ታወቀ::

በሌላ በኩል ደግሞ በነገው እለት በአጠቃላይ በሀገሪቱ ታላቅ የተቃውሞ ትእይንት በየመስኪዱ እንደሚደረግ ተገለጠ::

ምንጮቻችን ባደረሱን መረጃ መሰረት አሸባሪ በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ማእከላዊ ምርመራ በነበሩ ጊዜ በኤሌክትሪክ ወንበር አስቀምጠው ማሰቃየት ፡ የስለት ስብርባሪ ወለል ላይ በትነው በባዶ እግር ማስኬድ ፡ በገመድ አስረውና ዘቅዝቀው የመግረፍ ፡ ብልታቸውን በመግረፍ የማሰቃየት  ደርሶባቸዋል ብለዋል::

በሙስሊሞቹ አመራሮች ላይ ይህ ሁሉ በደልና ስቃይ የሚፈጸመው “እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ሰርተናል ብላችሁ እመኑ በሚል እንደሆነ ያመለከተው የምንጮቻችን መረጃ በሚደርስባቸው በዚህ ስቃይ የሚናገሩት ነገሮች በድብቅ ካሜራ እንደሚቀረጽም ገልጠዋል::

በዚህ መልኩ በታሳሪዎቹ ላይ በሚፈጸም ኢሰባአዊና የጭካኔ ተግባር አስገድደው እመኑ በማለት ለሚጠየቀው ጥያቄ የሚሰጡ መልሶችን በድብቅ ቀርጾ ለፍርድ ቤት በማስረጃነት በማቅረብ መንግስት የታወቀ ነው ያሉት ምንጮች በታሳሪዎቹ ላይ ጭካኔ የተመላበትን የማሰቃየት ተግባር የሚፈጽሙት ኮማንደር ተክላይ ፡ ምክትል ኮማንደር ከተማ ፡ ሳጅን ርእሶም ፡ ዮሴፍ የተባሉና ሌሎች አምስት ሰዎችን በስም ዝርዝር በመጥቀስ አጋልጦል:፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው እለት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተቀጥረው የነበሩት  በሚገኙት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት ፍርድ ቤት ሣይገኑ ተለዋጭ ቀጠሮ ለታህሳስ ስምንት እንደተሰጣቸው ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ አመልክቶል::

የማረሚያ ቤቱን ፖሊሶች ዋቢ ያደረጉት ምንጮቻችን የሚገኙት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር አባላት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አልተነገረንም ማለታቸውን ተናግረዋል::

በሌላ ዜና ደግሞ በመላው ሀገሪቱ ያሉ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት ታላቅ ተቃውሞ በነገው እለት ሊያደርግ መዘጋጀታቸውን ለማወቅ ተችሎል::

በነገው እለት በመላው ሀገሪቱ የተጠራው ይህ የተቃውሞ ትእይንት ቅዳሜ የሚከበረውን የብሄረሰቦች ቀንና ህገመንግስቱ የጸደቀበትን 18 ኛ አመት አስመልክቶ መንግስት የሀይማኖት ፡ የእምነትና ፡ የአመለካከት ነጻነትን የሚመለከተውን አንቀጽ 27 እንዲያከብር ለማሳሰብ መሆኑ ታውቆል::

በየመስኪዱ ይካሄዳል በተባለው በዚህ የተቃውሞ ትእይንት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል::