(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 19/2009)አዲስ አበባ በከፍተኛ የሃይል ርምጃና የደህንነቶች ወከባ ውስጥ ሆናም አድማውን አላቋረጠችም።
በማስፈራራት፣በማሸግና በማዋከብ የታጀበው የመንግስት ርምጃ በአንዳንድ ቦታዎች ውጤት እንዳላመጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ።በመርካቶ ዛሬም ያልተከፈቱ ሱቆችና መደብሮች መኖራቸውን የኢሳት ወኪል ካደረሰን መረጃ ማወቅ ተችሏል።
ዛሬ አየር ጤና በተባለው የአዲስ አበባ ክፍል ነጋዴዎች መደብሮቻቸውን በመዝጋት አድማውን ተቀላቅለዋል።
የመንግስት ታጣቂዎች አካባቢውን በመውረር በሃይል ሊያስከፍቱ ሞክረው እንደነበር የጠቀሰው ወኪላችን በነጋዴው የተባበረ አቋም ለጊዜው አልተሳካላቸውም ብሏል።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአየር ጤና በርካታ የንግድ ቦታዎች እንደተዘጉ ናቸው።
በመርካቶ በሃይል እንዲከፍቱ የተደረጉት ሱቆችና መደብሮች በቅርብ ቀናት ምላሽ ካልተገኘ ዳግም ሊዘጉ እንደሚችሉም አንዳንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነጋዴዎች ለወኪላቸው ገልጸዋል።
በሳሪስ፣ላፍቶ፣ቄራ አካባቢዎች ትላንት የተዘጉት የንግድ ቤቶች የተወሰኑት ዛሬም ስራ እንዳልጀምሩ ለማወቅ ተችሏል።
አድማው ተጠናክሮ እየተካሄደበት የሚገኘው የአማራ ክልሏ ሸበል በረንታ በአድማው ሳምንቷን ልትደፍን ነው።
ባለፈው ሀሙስ የሸበል በረንታ አድማ በተለይም ከትላንት በስተያ ሰባት ነጋዴዎች መታሰራቸውን ተከትሎ የተጠናከረ ሲሆን ዛሬም ድረስ የገበያ ቦታዎች ጭር እንዳሉ ናቸው።
ለወትሮው ቅዳሜና ረቡእ የሚቆመው የደውሃ ገበያ በዛሬው እለት በግዢና ሸማች አድማ ተመቶበት ያለሰው ባዶውን ውሏል።
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በርካታ መደብሮች ተዘግተው መዋላቸውን ለህወሃት መንግስት ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣም ዘግቧል።
ከሸበል በረንታ በተጨማሪ በሞጣና ቢቸና ነጋዴዎች ሱቃቸውን ሙሉ በሙሉ ዘግተዋል ሲል የምስራቅ ጎጃም ዞን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ሽፈራው አየለ መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ጠቅሷል።
በባህር ዳር ከተማ ትላንት የተወሰኑ መደብሮችና ሱቆች የተዘጉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በዛሬው እለትም የቀጠሉ አንዳንድ እንዳሉ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በደጀን ከተማም እንዲሁ ትላንት የተጠራው አድማ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ዛሬ ተግባራዊ አድርገውታል።
ደጀን ዛሬ ሙሉ በሙሉ ጭር ብላ የዋለች ሲሆን ነጋዴዎች አላግባብ የተጣለባቸው የቀን ገቢ ግብር እንዲሰረዝ አልያም በአድማው እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።
በወሎ ባቲ ለነጋዴዎች የቀን ገቢ ግምቱ ታድሏቸዋል።ነጋዴው በደረሰው ተመን መደናገጡንና ለተቃውሞ እየተነጋገር መሆኑን ማወቅ ተችሏል።
ወደ ባቲ ከተማ ግብር መስሪያ ቤት ሄደው የተሰጣቸው ምላሽ ተስፋ የሚያስቆርጥ በመሆኑ በቅርቡ የነጋዴዎች አድማ ሊመታ እንደሚችል ነው ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለከተው።
በሌላ በኩል በሐዋሳና በአርባምንጭ ከተሞች ትላንት ለሊቱን የአድማ ጥሪ መልእክት የያዙ ወረቀቶች መበተናቸው ታውቋል።
በሐዋሳ በቱሩፋት ኮንዲሚኒየም፣ በቤተሰብ መምሪያ፣በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደኢህዴን ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት፣በሐዋሳ ከተማ ፍርድ ቤት የማስታወቂያ ቦርድ ላይ እንዲሁም ዛሬ የሚከበረውን ንግስ ታሳቢ በማድረግ በሃዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ዙሪያም የአድማ ጥሪ ወረቀቶች መበተናቸውንና መለጠፋቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በአርባምንጭ በተመሳሳይ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ፣ በመነሃሪያ፣በጋሞ አዳባባይና በገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ወረቀቶች መበተናቸው ተገልጿል።
ህወሃት ኢህአዴግ በዘፈቀደ የሚጭንብንን ኢፍትሃዊ ግብር አንከፍልም ሸማቹ ህብረተሰብም በጋራ እንነሳ ለውሸታምና ቃላባይ አገዛዝ አንገብርም የሚሉ ጥሪዎችን የያዙት በራሪ ወረቀቶች እንዲሁም በፎቶግራፍ ተደግፎ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።