ዶክተር አቡነ ኤውስጣጢዎስወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ሲኖዶሱ ማሳሰቢያ ሰጠ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 19/2009)በሀገር ቤት የሚገኘውና በብጹእ አቡነ ማቲያስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ አቡነ ጳውሎስ ከነበሩበት ግቢ ከጥቅምት 30 2004 ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ 5 ደብዳቤዎችን መጻፉንና በስልክም ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉን አስታውቋል።

ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ በአቡነ ጳውሎስ ሲጠየቁ በስነ መለኮት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የነበሩት አቡነ ኤውስጣጢዎስ ትምህርቴን ጨርሼ እመለሳለሁ በማለታቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው እንዲመለሱ በሚደረግባቸው ግፊት አለመግባባት መፈጠሩን የቤተክህነት ምንጮች ይገልጻሉ።

በሰሜን አሜሪካ የካሊፎርኒያ ሊቀጳጳስ ሆነው ተሹመው ከ7 አመት በፊት ወደ አሜሪካ የገቡት አቡነ ኤውስጣጢዎስ ትምህርታቸውን አቋርጠው እንዲመለሱና ወደ ባሌ ሀገረ ስብከት እንዲዛወሩ ሲደረግ ችግሩ መባባሱም ተመልክቷል።

እሳቸውም የጀመርኩትን ትምህርት አላቋርጥም በማለታቸው የቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዳይሰጡ መደረጉና ደሞዛቸው መቋረጡንም መረዳት ተችሏል።

አቡነ ጳውሎስ ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ በኋላ እርሳቸውን ከተኳቸው አቡነ ማቲያስ ጋር ጤናማ ግንኙነት መስርተው የነበሩት አቡነ ኤውስጣጢዎስ ይሄ መልካም ግንኙነት በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ባሉ ሌላ አባት ጣልቃ ገብነት ችግር ስለገጠመው ችግሩ ሳይፈታ መቀጠሉን የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ።

ብጹእ አቡነ ኤውስጣጢዎስ በምርጫ 1997 ማግስት 199 ሰዎች የተገደሉበትን ሁኔታ እንዲያጣራ የተሰየመው አጣሪ ኮሚሽን አባል ነበሩ።

በወቅቱም የመንግስት ርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም ብለው ድምጻቸውን ከሰጡት 9 የኮሚሽኑ አባላት አንዱ የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ተመጣጣኝ ብለው የመንግስትን ርምጃ የደገፉት ኤልያስ ኑርና መኮንን ደሳሳ ብቻ ነበሩ ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሁሉንም የኮሚሽኑን አባላት ቤተመንግስት ጠርተው ማስፈራሪያ ከሰጧቸው በኋላ አቡነ ጳውሎስም በግል ጠርተው አቋማቸውን እንዲቀይሩ በማስፈራራትና በማግባባት ተመጣጣኝ ነው ብለው እንዲፈርሙ እንዳደረጓቸው የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

ተመጣጣኝ ነው ብለው የያዙትን አቋም በተጽእኖ እንዲቀይሩ ከተደረጉት ውስጥ ዶክተር ገመቹ መገርሳ፣ቄስ ደረጄ ጀንበሩና አቡነ ኤውስጣጢዎስ ይጠቀሳሉ።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር አቶ ፍሬህይወት ሳሙኤልና ምክትላቸው አቶ ወልደሚካኤል መሸሻ ዋናውን ሪፖርትና የድምጽና የምስል ማስረጃ ይዘው አቋማቸውን ሳይቀይሩ ከሀገር መውጣታቸው ይታወሳል።

ሌላው የኮሚሽኑ አባል አቶ ምትኩ ተሾመም ድርጊቱን በማውገዝ ከሀገር መሰደዳቸው ይታወሳል።