ታህሳስ 13 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጋሞጎፋ ዞን በጨንቻ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች መሬታቸው ያለ አግባብ በመነጠቁ ሳቢያ ከመንግስት ሹመኞችና ፖሊሶች ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ።
አርሶ አደሮቹ ወደ ግጭት ለመግባት የተገደዱት፤”የጨንቻ ከተማን ለማስፋት” በሚል ሰበብ እየተካሄደ ባለው የከተማ ማካለል ስራ፤ ከይዞታቸው አላግባብ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ በመገንዘባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ሰንደቅ እንደዘገበው፤በከተማዋ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶአደሮች የከተማዋን መስፋፋት በመሠረቱ ባይቃወሙም፤ ተገቢው የሞራልና የገንዘብ ካሳ ሳይከፈላቸው የማካለሉ ሥራ መጀመሩ ተገቢ አለመሆኑን ገልፀዋል።
ሰሞኑንም ያለበቂ ውይይት የከተማው አስተዳደር ችካል በመቸከል የማካለል ተግባሩን በሚፈፀምበት ወቅት፤ ከአርሶ አደሮቹ ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
የጨንቻ ከተማ ከንቲባ የከተማዋን ድንበር እንደገና የማስፋቱና የማካለሉ ሥራ እየተከናወነ ያለው፤ የክልሉና የዞኑ እቅድ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ከንቲባው አክለውም ጨንቻ ከሚሰፉት ከተሞች አንዷ ብትሆንም፤ “የከተማ ማስፋት ስራ ሲካሄድ አርሶ አደሩን እያፈናቀልን አይደለም ሲሉ” አስተባብለዋል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል
‘‘ሥራው ውስጥ ገና አልገባንም። ገና የማወያየት ሥራ ይጠብቀናል። ከመሬት አጠቃቀም ጋር ያሉ ችግሮችን ከህብረተሰቡ ጋር እናወያያለን። አሁን ላይ የማካለል ሥራ ቢከናወንም አርሶ አደሩን የያዘው መሬት ትናንት እንደያዘው ሁሉ ዛሬም ወደፊት ይዞ የሚቀጥልበትን አግባብ እንዳለ ገልፀናል። ለአርሶ አደሩ የሚሰጥ የመሬት ልኬት ካርድ እየተሰጠ ነው’’ ሲሉ ከንቲባ አይናለም ገልፀዋል።
ከንቲባው የአርሶ አደሮቹን ቅሬታ የከተማው አስተዳደር ከወረዳውና ከዞኑ ጋር ለመፍታት እየሞከረ መሆኑን ቢገልፁም፤ አርሶ አደሮቹ ግን በውርስና በስጦታ ያገኙት የመሬት ይዞታ ሕጉን ባልተከተለ መንገድ እየተነጠቁ መሆኑን በመግለጽ የከንቲባውን ማስተባበያ ውሸት እንደሆነ አጋልጠዋል ።
በከተማዋ በቂ ግንባታ በሌለበት ሁኔታ መሬት ለማካለል የተደረገው ሩጫ የአርሶ አደሩን መሬት አላግባብ ለመንጠቅ ነው ሲሉም ስጋታቸውን ገልፀዋል።
“መሬታችንን አናካልልም” ካሉ አርሶ አደሮች ጋር በተነሳ ብጥብጥ አንዳንድ አርሶ አደሮች መደብደባቸውን በብጥብጡ ወቅት በአካባቢው ከነበሩ የአይን እማኞች ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።
ኢሳት በአካባቢው የተነሳውን ግንጭት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።