ለርዮት አለሙ መከላከያ ምስክር ሆኖ በመቅረብ የመሰከረላት ሀይለ መስቅል በሸዋምየለህ ላይ የደህንነት ሰራተኛ ነን ያሉ 3 ግለሰቦች ከባድ ማስፈራራያ አደረሱበት

12 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በትላንትናው እለት በ11/04/04ዓ.ም ለፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ርዮት አለሙ መከላከያ ምስክር ሆኖ በመቅረብ የመሰከረላት የፍትህ አዘጋጅ ሀይለመስቅል በሸዋምየለህ ከምሽቱ 12፡30 ላይ ቢሮ በር ላይ የደህንነት ሰራተኛ ነን ያሉ 3 ግለሰቦች  ሲም ካርዱን ከነጠቁ በኋላ ከባድ ማስፈራራያ እንዳደረሱበት ታወቀ
በዚሁ እለት ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ የፍትህ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ እና ሀይለመስቀል በሸዋምየለህ ከቢሮ ወጥተው ሲሄዱ በርከት ያሉ የደህንነት አባሎች ሲከታተሏቸው ከቆዩ በኋላ ሁለቱም ጋዜጠኞች ወደ ተመስገን መኖሪያ ቤት ሲሄዱ የሚከታተሏቸው ሰዎችም አብረው በመሄድ አካባቢውን ከበው ያደሩ ሲሆን በዛሬው እለትም ክትትሉ መቀጠሉ ታውቋል፡፡

አሁን እየተደረገ ያለው ማስፈራሪያና ክትትል ከመጠን ያለፈ ከመሆኑም በላይ በስራቸው ላይ ጫና እያሳደረባቸው መሆኑን ጋዜጠኞቹ በፍትህ ድህረ ገፅ ላይ ባሰፈሩት ሰበር ዜና ገልጸዋል፡፡

የመለስ መንግስት ኢትዮጵያውያን በሀሰት እንዲመስክሩ እያስገደደ፣ አንመሰክርም ያሉት ወይም ለእስረኞቹ የመሰከሩትን ደግሞ እያስፈራራ መሆኑን መግለጣችን ይታወሳል። በጋዜጠኞች ላይ የሚደረገው ወከባ አገዛዙ ያለበትን ውጥረት እንደሚያሳይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለኢሳት መናገሩ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሲፒጄ በስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈውን ብይን ተቃውመዋል:: ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋ “ሁለቱ ስዊዲናውያን ጋዜጠኞች ከአሸባሪዎች ጋር መተባበራቸው ተረጋግጧል” በማለት የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠታቸው፣ የአለማቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት የደረሰበትን ደረጃም አመላክቷል።

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ስለ አሸባሪዎች ዘገባ በማቅረብ እና አሸባሪዎችን በመርዳት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት  አልቻለም” ብሎአል።

“ኢትዮጵያ ትክክለኛ የሆነ የሽብር ስጋት እንዳለባት እናምናለን” የሚለው የስቴት ዲፓርትመንት መግለጫ፣ “ይሁን እንጅ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ ባደረግነው ውይይት ላይ እንደገለጥነው፣ ነጻ ሚዲያ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ዋነኛው አካል  ሊሆን እንደሚገባ መግለጥ እንወዳለን” ሲል የመለስን መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዝ በተዘዋዋሪ መንገድ ተችቷል።

የአሜሪካ መንግስት የጋዜጠኞችን ጉዳይ በተመለከተ ሁኔታውን እንደሚከታተለውና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚያደርገውን ውይይት እንደሚቀጥል ተናግሯል።

አምነስቲ ኢንትርናሽናል በበኩሉ የስዊድ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።

ማርቲን ሺቢየና ጆሀን ፔርሰን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባርን ስለመርዳታቸው በቂ ማረጋገጫ ሊገኝ አለመቻሉን የገለጠው አምነስቲ፣ ጋዜጠኞቹ የህሊና እስረኞች ናቸው ብሎአል። 

አምነስቲ ” የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የጸረ ሽብርተኝነትን ህግ ሀሳብን በነጻነት የመግለጥን መብት ለመጨፍለቅ እየተጠቀሙበት ” ሲል ወቀሳ አቅርቧል።

ሶስት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በተመሳሳይ ወንጀል መከሰሳቸውን ያስታወሰው አምነስቲ፣ አሁን በጋዜጠኞች ላይ የሚደረስው እስራትና እንግልት መንግስት እንዲዘገብ የማይፈልገውን ነገር አፍኖ ለማስቀረት ለማድረግ ነው ብሎአል።

የአለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ፤ ሲፒጄ፣ በበኩሉ ጋዜጠኞቹ በፖለቲካ ሰበብ  እንጅ ሽብረተኞችን በመርዳት አለመታሰራቸውን በመጥቀስ፣ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጠይቋል።

የመለስ መንግስት  በአረብ አገራት የታየው አብዮት በአገሩም ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት ጋዜጠኞችን ማሰሩን ሲፒጄ  ዘግቧል።