ህዳር 25 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአካባቢው የሚኖሩት የጋሞ ተወላጆች ተቃውሞውን ያነሱት፣ የእርሻ ማሳቸውን ወደ ከተማ ለማካለል ሙከራ ማድረጉን ለመቃወም ነው።
ከሁለት ቀናት በፊት 5 ሺ የሚጠጉ ነዋሪዎች ለተቃውሞ ሰልፍ በወጡበት ጊዜ የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ተገኝተው ሰልፉን የበተኑ ሲሆን፣ መንግስትም በአካባቢው የስልክ ግንኙነት እንዳይኖር አድርጎ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ውጥረቱ አሁንም እንዳለ መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ ህዝቡ ሰልፉ ከተበተነ በሁዋላም ተቃውሞውን እያሰማ ነው። ምንጮች እንደሚሉት የመንግስት ካድሬዎች ሳይቀር በሰለማዊ ሰልፉ ላይ ተገኝተው ነበር።ጨንቻ ከተማ ከአርባ ምንጭ 38 ኪሎሜትር ትርቃለች።
በመላ አገሪቱ የሚታው ውጥረት አሁንም እንደጨመረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኑሮ ውድነቱና የአስተዳደር በደሉ መጨመር ህዝቡን ለተቃውሞ ሊያስነሳው እንደሚችል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በቅርቡ ለኢሳት መናገራቸው ይታወሳል።
አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ከአረቡ አለም አብዮት የሚማሩት ነገር እንደሌለና የአረቡ አይነት አብዮት በኢትዮጵያ ከ20 አመታት በፊት መካሄዱን ገልጠዋል።
ከአረቡ አብዮት በሁዋላ ተቃዋሚዎቻቸውን በሽብርተኝነት ስም ወይኒ የወረወሩት አቶ መለስ፣ አብዮት ይነሳል ብለን እንቅልፍ አጥተን አናድርም እያሉ በአደባባይ ቢናገሩም፣ በተግባር እየታዬ ያለው የዚህ ተቃራኒ መሆኑን በአገር ውስጥ የሚታየው የተጠናከረ ወታደራዊ ጥበቃ ምስክር ነው የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ።