የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ኮሚቴዎች በባህር ዳር ተገናኝተዉ መነጋገራቸዉን ቪዢን ዴይሊ የተሰኘዉ የሱዳን የሚዲያ ማእከል ገለጸ

 ህዳር 26 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ኮሚቴዉ በድንበር አካባቢ በድብቅ የሚካሄደዉን የጦር መሳሪያ ዝዉዉር ለመግታት፤ አዘዋዋሪዎቹን ለመያዝና ለማሰር፤ በድንበሩ አካባቢ ያሉ ትናንሽ ከተማዎችና ወረዳዎች በፀጥታ ጥበቃ ረገድ ይበልጥ በሚጠናከሩበት፤ እና መረጃ በሚለዋወጡበት መንገድ ላይ መክሯል።

 እንዲሁም የቀንድ ከብት በሽታዎችን ለመቆጣጠርና የእንሰሳት የህክምና መስጫ ጣቢዎችን ለማቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸዉ ተገልጿል። 

 የሱዳን የድንበር ኮሚቴ የተመራዉ ያልተማከለዉ የመንግስት ም/ቤት ዋና ፀሃፊ በሆኑት ፕሮፌሰር አል አሚን ዳፋ አላህ ሲሆን የኢትዮጵያን ኮሚቴ የመሩት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አያሌዉ ጎበዜ ናቸዉ። 

የአማራዉ ክልል ፕሬዝዳንት “የሰላም ጠላቶች “ ባሏቸዉ ላይ ሁለቱ አገሮች በድንበር አካባቢ በጋራ ለመስራት የደረሱበት ስምምነት እንዳስደሰታቸዉና “አሽራፍ” የተሰኘዉ የስጋ ዉጤቶች ኩባንያን ጨምሮ የሱዳን ባለሃብቶች በአማራ ክልል ዉስጥ ኢንቬስት እንዲያደርጉ ከታክስ ነፃ እንዲሆኑና ሌሎች ማበረታቻ የተደረገላቸዉን መሆኑን በመዘርዘር መናገራቸዉን የዜና ምንጩ ጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ በቱሪዝም መስክ የሱዳን አገር ጎብኚዎች የጥቁር አባይ ምንጭ የሆነዉን የጣና ሃይቅንና ሌሎች የክልሉን ታሪካዊ ስፍራዎች ለመጎብኘት እንዲችሉ ጥሪ አድርገዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሰት ከመተማ እስከ ጋምቤላ ጠረፍ ድረስ ከ1 ሺ 600 ኪሎ ሜትር በላይ ቁመትና ከ30-50 ኪሎ ሜትር ጎን በላይ ያለዉን ሰፊ ታሪካዊ ለም መሬት ለሱዳን መንግስት አሳልፎ የሰጠና በምትኩ የሱዳን መንግሰት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የተመዘገቡ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ስደተኞችን ለጠ/ሚኒስትር መለስ መንግሰት አሳልፎ በመስጠት ላይ እንዳለ ይታወቃል። 

የክልሉ መሬት በህገወጥ መንገድ ለሱዳን ተላልፎ ከመሰጠቱ በላይ በመሬቱ ላይ የነበሩት ድሃ አርሶ አደሮችና ከዉጭ አገር የመጡ ኢትዮጵያዊያን ኢንቬስተሮች ድንበር ጥሶ በገባ የታጠቀ የሱዳን የፀጥታ ሰራዊት በሃይል ተይዘዉ ካርቱም ድረስ ተወስደዉ ወህኒ ቤት እንዲማቅቁ ሲደረግ ፣ ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ ብአዴን/ በሚል ስም የተቋቋመዉ በህወሃት ተለጣፊነቱ የሚታወቀዉ የአማራዉ ድርጅትና ጊዜያዊ ስልጣንና ጥቅም የገዛቸዉ አያሌዉ ጎበዜን የመሳሰሉ የክልሉ ባለስልጣናት አንዳችም ቃል እንዳልተነፈሱ ይታወሳል ሲል ንጉሴ ጋማ ከለንደን ዘግቧል።