በጋሞጎፋ ዞን በተነሳው ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታሰሩ ብዙዎችም ተደበደቡ

ሐምሌ ፩( አንድ )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-እሁድ ሰኔ 30፣ 2005 ዓም በደቡብ ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ በሰላም በር ከተማና አካባቢዋ የሚኖሩ ከ7 ሺ በላይ ነዋሪዎች፣ የታሰሩ መሪዎቻችን ይፈቱትልን የሚል ጥያቄያቸውን በወረዳ ጽህፈት ቤት ተገኝተው ለማቅረብ በተጓዙበት ወቅት የዞንና የወረዳ ፖሊሶች በነዋሪዎቹ ላይ ድበደባ መፈጸማቸውን 300 የሚሆኑትን   ደግሞ ማሰራቸውን ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።

አንዳንድ ቤተሰቦች ለኢሳት እንደገለጹት ፖሊሶች እድሜያቸው ከ13 አመት በላይ የሆኑ ልጃገረዶችንና ወንዶችን ሳይቀር ከቤታቸው እያወጡ በመደብደብ አስረዋቸዋል።  አቶ ብርሀኑ የተባሉ ነዋሪ ፖሊሶች የፈጸሙት ድርጊት ጨካኝ በሚባለው የደረግ ስርአት ጊዜ እንኳን ያልታየ ነው ብለዋል ። የችግሩን አሳሳቢነት ለክልል ባለስልጣናት ለማስረዳት  አዋሳ ከሚገኙት የአገር ሽማግሌዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መሰቦ ማዳልጮ  እንደተናገሩት ፖሊሶቹ እርምጃውን የወሰዱት ጥያቄያቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ በመሰባሰብ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው ።

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የእስረኞች ጠባቂ ፖሊስ እንደተናገረው  300 የሚሆኑ እስረኞች በአንድ ክፍል ውስጥ  ታጉረው የሚገኙ ሲሆን፣ ፖሊስ በዛሬው እለት ፍርድ ቤት ቢያቀርባቸውም፣ እስረኞቹ ግን በወረዳው ፍርድ ቤት ላይ እምነት የለንም በሚል ጥለው መውጣታቸውን ገልጿል።  በድብደባው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ወጣቶች ህክምና እንደተከለከሉም ተናግሯል።

የአካባቢው ተወላጅ የአንድነት ፓርቲ የደቡብ ተወካይ የሆነው አቶ ዳንኤል ሽበሺ እንደገለጸው ችግሩ የተፈጠረው መንግስት የቀረበለትን የማንነት፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ባለመቻሉ ነው።

በሰላም በር ከተማ ዛሬ ሀምሌ 1፣  ከመከላከያ ሰራዊት  ፣ ከልዩ ሀይሎችና ከአካባቢው ፖሊሶች በስተቀር  በከተማ የሚንቀሳቀስ ሰው አለመመልከታቸውን አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳው አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ የስጋት ስንታን ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም ስብሰባ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ሳይሰካልን ቀርቷል።