50 ኢንዱስትሪዎች በሀይል እጥረት ስራ አልጀመሩም ተባለ

ሐምሌ ፩( አንድ )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ ተጎራባች በሆነችው ገላን ከተማ ውስጥ 50 ኢንዱስትሪዎች በኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያት ሥራ አለመጀመራቸውን ሪፖርተር ዘገበ።

የከተማው ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ከበደ የሀይል አቅርቦቱ ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

‹‹በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት ግንባታ ጨርሰው ወደ ሥራ የገቡ ባለሀብቶች ለሞራል ውድቀት እየተዳረጉ ነው፤›› ያሉት ከንቲባው፣  የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሥራ ውስጥ የገቡትን ባለሀብቶች ጭምር እየጎዳ መሆኑንም ገልጸዋል።

አንድ በእምነበረድ ማውጣት ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብት በተደጋጋሚ በሚፈጠር የኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚያመርቱት  ምርት እየተበላሸ ኪሳራ ውስጥ መግባታቸው ተናግረዋል።

ሌላ ባለሀብትም በኤሌክትሪክ ምክንያት ለስምንት ወር ያህል ያለሥራ ለተቀመጡ ሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈላቸውን አስረድተዋል፡

ፋብሪካቸው የሚያመርተውን ጨርቃ ጨርቅ በቀጥታ ወደውጭ እንደሚልኩ የገለጹ አንድ ባለሀብት ደግሞ በዚሁ የኃይል ችግርና መቆራረጥ ምክንያት በቅርቡ ለሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ለመገንባት ባለመቻላቸው ከሁለት መቶ በላይ ሠራተኞች እንደቀነሱ ገልጸዋል፡፡

ለጋዜጣው  አስተያየት የሰጡ   ባለሀብቶች ተስፋ እየቆረጡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።