በጋምቤላ የባጃጅ አገልግሎት ተቋረጠ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2010)

ጋምቤላ ከተማ የባጃጅ ታክሲ አገልግሎት መቋረጡ ተገለጸ።

ፋይል

ከፍተኛ ግብር ተጭኖብናል ያሉት የታክሲ አሽከርካሪዎቹ ከዛሬ ጀምሮ ስራ ማቆማቸውን ነው ሪፖርተር ጋዜጣ የዘገበው። እነዚህ ለጋምቤላ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ባጃጆች ዛሬ ረቡዕ ከጠዋት ጀምሮ አገልግሎት ማቆማቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህም የተነሳ ነዋሪዎች ትራንስፖርት መቸገራቸው ታውቋል።

የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡት የባጃጅ ሾፌሮቹ የተጣለብን ግብር ከአቅማችን በላይ በመሆኑ መክፈል አንችልም ማለታቸው ተጠቅሷል። በጉዳዩ ላይ የከተማዋ አመራሮች ውይይት ለማድረግ እየተዘጋጁ እንደሆነ ቢገልጽም ሹፌሮቹ ተገቢውን ምላሽ እስከምናገኝ ስራ አንጀምርም ብለዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በጋምቤላ በተበተነ የአድማ ጥሪ ህዝብ በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ እንዲያደርግ ተጠይቆ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

የጋምቤላ ክልል መንግስት ለሰራተኞች ደምወዝ የሚከፍለው በማጣት ከሁለት ወራት በላይ መቆየቱን በመጥቀስ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። በባጃጅ ታክሲዎች ላይ ከአቅም በላይ ግብር የተጣለው ይህንኑ ብድር ለመክፈል ሊሆን ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ።