መጋቢት ፳፬ (ሃይ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በጋምቤላ በቅርቡ 19 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊቱ ገዳዮችን ለማደን ከፍተኛ ዘመቻ ሲያካሂድ ቢቆይም እስካሁን ድረስ አልተሳካለትም። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዘመቻው አንድም ሽፍታ ያልተያዘ በመሆኑ ሰራዊቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ሽፍቶቹን አውጡ በማለት እያሰቃዩ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት በጋምቤላ ጸጥታ የማስከበሩን ሀላፊነት ከክልሉ መንግስት ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቡ ላይ የሚፈጸመው ግፍ ከፍተኛ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጠዋል። ነዋሪዎች ሽፍቶችን አውጡ እየተባሉ ይደበደባሉ፣ ይገደላሉ። ኢሳት ለማረጋጋጥ ባይችልም የመከላከያ ሰራዊት አባለት በኡኩና፣ አቦቦ፣ ፒንዮዶ እና ኢታንግ መንደሮች ከ40 ያላነሱ ሰዎችን መግደላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡበ ሱዳን መንግስትና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ሰሞኑን ጋምቤላ ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቋል። የውስጥ ምንጮች እንዳሉት በሁለቱ መንግስታት መካከል ቅዳሜ እለት እስከ ሌሊቱ 6 ሰአት የዘለቀ ውይይት ቢካሄድም በመሰረታዊ ጉዳይ ላይ ሳይስማሙ ተለያይተዋል። በአቶ መለስ አማካሪ በአለቃ ጸጋየ የተመራው የልኡካን ቡድን የደቡብ ሱዳን መንግስት ወደ ሁለቱ አገሮች እየተመላለሱ ስራ የሚሰሩት የኑዌር ተወላጆችን እንዲያስቆም፣ እንዲሁም በወንጀል የሚጠረጠሩትን አሳልፎ እንዲሰጥ ቢጠይቁም ፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ግን ሳይቀበለው ቀርቷል።
ወደ ሁለቱ አገሮች እየተመላለሱ ስራ የሚሰሩት በተለይም የኑዌር ተወላጆች የጸጥታ ችግር ይፈጥራሉ የሚል አቋም የያዘው መንግስት፣ የደቡብ ሱዳን አቻውን ለማሳመን ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም። በሁለቱ አገሮች መካከል የሚገን አንድ የስደተኞች ካምፕ ግን እንዲዘጋ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ዘጋቢያችን እንዳለው በከተማው ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ነው። ላለፉት ሁለት ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው መምህራን ዛሬም የስራ ማቆም እድማ አድርገው ውለዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide