በጋምቤላ ክልል በብሄር ግጭት የብዙ ሰው ህይወት ጠፋ፣ ክልሉ በፌዴራል መንግስት ቁጥጥር ስር ውሏል

ኢሳት (ጥር ፥ 20 2008)

በጋምቤላ ክልል በተነሳ የብሄር ግጭት በክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊን ጨምሮ ከ12 ሰዎች በላይ መገደላቸው ተሰማ።

በትናንትናው ዕለት በጋምቤላ ከተማ መምህራን ኮሌጅ አካባቢ ቦምብ ፈንድቶ ባሮ ወንዝ የሚሄድ የአኝዋክ ብሄር ተወላጅ ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ በከተማዋ በአኙዋክና ኑዌር ብሄር ተወላጅ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ግጭት ተከስቶ እንደነበረ የኢሳት ምንጮች ከስፍራው ዘግበዋል።

ግጭቱን ተከትሎ የታጠቁ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት በወሰዱት የሃይል እርምጃ አራት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሰባት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ታውቋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በጆሮ ወረዳ በጠመንጃ በታገዘ የእርስ-በዕርስ ግጭት አምስት የኑዌርና ሁለት የአኙዋክ ብሄር ተወላጆች ላይ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።

ሃሙስ ጥር 20 ታጣቂዎች ከፉኚዶ ወደ ጋምቤላ ሲጓዙ በነበሩት የክልሉ የትራስፖርት ቢሮ ሃላፊ ላይ በወሰዱት የበቀል እርምጃ ሃላፊው እንደተገደሉ ለመረዳት ተችሏል። ሃላፊው የኑዌር ብሄር ተወላጅ እንደእንደነበሩ፣ ግድያውን የፈጸሙት የአኙዋክ ወጣቶች መሆናቸውን መረጃው ለኢሳት የላኩት ምንጮች ገልጸዋል።

በሁለቱ ብሄሮች መካከል ተመሳሳይ ግጭቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተደጋገሙ መምጣታቸውን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦሌሮ ኦፒዮ ሾፌር በሆኑ የአኝዋክ ተወላጅና የኮሌጁ ምክትል ዲን በሆኑ የኑዌር ተወላጅ መካከል በመሬት በተነሳ ግጭት ሾፌሩ በጥይት ተመትቶ ቆስሏል።

ከአንድ ወር በፊት የአኝዋክና ኑዌር ባልና ሚስት መካከል በትዳራቸው ውስጥ በተፈጠረ ግጭት ሁለቱም ሲገደሉ፣ ግጭቱ ከባልና ሚስት ቤተሰቦች አልፎ ወደ ሁለቱ ብሄር ተወላጆች በመዛመቱ መንደሮች ተቃጥለው የሰው ህይወት ጠፍቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በደቡብ ሱዳን መንግስት ውስጥ በተፈጠረው ቀውስ፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ለመዋጋት መሳሪያ ይዞ በጋምቤላ አካባቢ የሚንቀሳቀሰውና በኢትዮጵያ መንግስት የሚደገፈው ሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን ለግጭቱ መባባስ የራሱን አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።

ከመሬት ቅርምት ጋር በተያያዘ የጋምቤላ ተወላጆች በስርዓቱ ላይ በተለይም እዚያ ስፍራ እርሻ በያዙ የህወሃት ታጋዮች ላይ ተቃውሞ ማንሳታቸውን ተከትሎ በሁለቱ የጋምቤላ ብሄረሰቦች መካከል ግጭቶች እንዲፈጠሩ የተቀነባበሩ ሙከራዎች እንዲካሄዱ መቆየታቸውንም መረዳት ተችሏል።

ግለሰባዊ ግጭቶች ወደ ብሄር ግጭት ኣንዲያመሩ የተቀነባበሩ ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን የሚገልጹት ምንጮች በስልጣን ላይ ያለ የኑዌርና የአኝዋክ ተወላጆች ከስርዓቱ የደህንነት ሰዎች ጋር በመሆን ግጭቱ እንዲስፋፋ በመስራት ላይ መሆናቸውንም ተመልክቷል።

በጋምቤላ አካባቢ እየተካሄደ ያለውን የመሬት ወረራ በመቃወም በአጠቃላይ ስልጣን ላይ ያለው ቡድን አካባቢውን እንዲለቅና በኢትዮጵያ ሌላ የፖለቲካ ስራ እንዲዘረጋ ነፍጥ ያነሱ የጋምቤላ ድርጅቶች በአንድ ጥላ ስር መሰብሰብ መጀመራቸው ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ያላስደሰተ ዕርምጃ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

እነዚህ የጋምቤላ ድርጅቶች አርበኞች ግንቦት 7ትን ለመሳሰሉ ህብረ-ብሄር ሃይሎች ጋር መስራት መጀመራቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በጋምቤላ የዘር ግጭት ሲቀሰቀስ የተሰባሰቡት የጋምቤላ ሃይሎች በዘር መስመር ይሰነጠቃሉ በሚል ስሌት ስለመቀነባበራቸው የሚገልጹ ወገኖች አሉ።

አሁን የደረሰን ዜና እንደሚያመለክተው በጋምቤላ ክልል ማረሚያ ቤት በደረሰ ጥቃት ከ9 የሚበልጡ ሰዎች እንደተገደሉ ታውቋል።

የፌዴራል መንግስትም ክልሉን እንደተቆጣጠረው ታውቋል።