ኢሳት (ሚያዚያ 13 ፥ 2008)
ባለፈው ሳምንት በጋምቤላ ክልል ተፈጽሞ በነበረው ጥቃት ታፍነው የተወሰዱ ከ100 በላይ ህጻናት ያሉበት ስፍራ ታውቋል ቢባልም በአካባቢው የተወሰደ ወታደራዊ እርምጃ አለመኖሩን የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ሃሙስ ዘገቡ።
ጥቃቱን ከደቡብ ሱዳን መነግስት ጋር በጋራ ለማካሄድ ምክክር በማካሄድ ላይ ሲሆን በዚሁ ጥቃት ልጆቻቸው ታፍነው የተወሰዱባቸው ወላጆች በበኩላቸው ልጆቻቸውን በህይወት እናገኛለን የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ህጻናቱ በህይወት ለመታደግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት የመንግስት ባለስልጣናት ወደ 125 አካባቢ የሚደርሱ ህጻናት በቅርቡ ነጻ ይለቀቃሉ ሲሉም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ ጥቃት ባለቤታቸውን ያጡና ሶስት ልጆቻቸው ታግተው የተወሰደባቸው አንድ እናት በበኩላቸው ልጆቻቸውን መልሶ የማየት ተስፋ እንደሌላቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ቶል ማሉላ የተባሉ እናት ልጆቻቸው በተኩስ ልውውጡ ወቅት ይገደሉ አልያም አሁንም ድረስ በጣታቂዎች ስር ይሁኑ የተረጋገጠ መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
አብዛኛው የኑዌር ጎሳ የሆኑት አባላት በተገደሉበት በዚሁ ጥቃት ከ200 የሚበልጡ ሰዎች ተገድለው ወደ 100 የሚጠጉ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት አርብ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት ከ20ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎችም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ነዋሪዎቹ ዳግም የጥቃት ሰለባ እንሆናለን የሚል ስጋር እንዳለባቸውም ለመረዳት ተችሏል።
ወደደቡብ ሱዳን ግዛት ለመግባት ከሃገሪቱ መንግስት ፈቃድን ሲጠባባቅ የነበረው የኢትዮጵያ መከላከላያ ሰራዊትም ይሁንታን አግኝቶ ለጥቃቱ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በታጣቂዎች ጥቃት ሃዘናቸውን በሰላማዊ ሰልፍ የገለጹት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው መንግስት ጥበቃን እንዲያደርግላቸውና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትም በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የሙርሌ ታጣቂዎች በሃገሪቱ ካሉ ታጣቂ አንጃዎች መካከል ጠንካራው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሲሆን የደቡብ ሱዳን መንግስት ታጣቂዎችን መሳሪያ ለማስፈታት ሲያካሄድ የነበረው ዘመቻ ሳይሳካለት መቅረቱም ታውቋል።