ታንዛኒያ 74 ኢትዮጵያውያንን ወደኬንያ ድንበር አባረረች

ኢሳት (ሚያዚያ 13 ፥ 2008)

በቅርቡ ወደሃገሯ በሚገቡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መጨመር ስጋቷን ስትገልፅ የቆየችው ታንዛኒያ 74 ኢትዮጵያውያንን በኬንያ ድንበር አሰፈረች (ጣለች)።

የታንዛኒያ መንግስት ማክሰኞ የወሰደው ይህንኑ እርምጃ ተከትሎም በሃገሪቱና በኬንያ መንስታት በኩል ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት መፍጠሩ ታውቋል።

”ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደሃገራቸው መመለስ ሲገባቸው በኬንያ ድንበር መጣላቸው ተገቢ አይደለም ስትል ኬንያ በታንዛኒያ መንግስት ላይ ተቃውሞዋን እንደገለጸች ኒውስ 24 የተሰኘ ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።

በድርጊቱ ተቃውሞዋን ያሰማችው ኬንያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ታንዛኒያ እንደምትመልስም ማስታወቋን ዘ-ስታንዳርድ ጋዜጣ አስነብቧል።

“ኬንያ በአለም አቀፍ ህግ-ቢሆንም የታንዛኒያ ችግር የመሸከም ግዴታ የለባትም” ሲል የኬንያ የኢሚግሬሽን ባለስልጣን አስታውቋል።

74ቱ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ታንዛኒያ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ለእስር ተዳርገው የነበሩ ሲሆን ሃገሪቱ ስደተኞችን ከእስር በመልቀቅ በሌላ ሃገር ድንበር መጣሏ ተቃውሞን ቀስቅሷል።

ካለፈው አራት ወር ወዲህ ወደታንዛኒያ የሚገቡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በመጨመር ላይ መሆኑን የሚገልጹት የታንዛኒያ ባለስልጣናት ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በሃገሪቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በእስር ቤት የሚገኙ ሲሆን፣ ታንዛኒያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በእንዲህ ያለ እርምጃ ስትወስድም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

በኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ዙሪያ ታንዛኒያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የሚገኙ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

ከታንዛኒያ በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጎረቤት ማላዊ፣ ናሚቢያና፣ ዜምባቡዌም የሚገኙ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ እነዚህን ሃገራት በመጠቀም ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ  እንደነበሩም ይነገራራል።