(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2011)በጋምቤላ በድብቅ የተገኙትና በመከላከያ እየፈረሱ ያሉት ካምፖች በደቡብ ሱዳኑ ተቀናቃኝ ሬክ ማቻር ቡድን የሚመራ ሃይል የገነባው መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመለከተ።
እንደመረጃው ከሆነም በካምፑ የተገኙትና በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ታጣቂዎች ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ ነው የሚል መታወቂያ በኪሳቸው መገኘቱም ታውቋል።
ይህን ተከትሎም በጋምቤላ ያለው አለመረጋጋት መቀጠሉ ነው የታወቀው።
የአኝዋክ ሬዲዮ አዘጋጁ አግዋ ጊሎ ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ሁኔታ ውስጥ የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስቱ ምንም እያደረጉ አለመሆናቸውን ችግሩን የከፋ አድርጎታል ብሏል ከኢሳት ጋር በነበረው ቆይታ ።
በየቀኑ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ፣ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻላቸው በራሱ ሌላ ፈተና ነው ብሏል።
በካምፕ ውስጥ ያሉት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች አብዛኞቹ መሳሪያ የታጠቁ ናቸው ይላል አቶ አግዋ።ነገር ግን መሳሪያውን ማን እንዳስታጠቃቸው አይታወቅም።
ሰባት የስደተኞች ካምፖች አሉ።እነዚህ ካምፖች ደግሞ በአንድ ቦታ ብቻ እንዲሆኑ መደረጉ ችግሩችን እንዲባባስ አድርጎታል ባይ ነው።
እንደ አግዋ ጊሎ አባባል የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ መፍትሄ የማያመጡ ከሆነ የክልሉ የጸጥታ ሃይል የራሱን ርምጃ መውሰድ አለበት ባይ ናቸው።