በጋምቤላ ክልል ጎደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ አካባቢ ሰሞኑን በተቀሰቀሰ ግጭት አምስት ሰዎች መሞታቸውን የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል ።
በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ማጣታቸውን የሚናገሩት የወረዳው ነዋሪዎች የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ጥያቄዎችን ባነሱ ነዋሪዎች ላይ የሚወስዱት እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል ።
በተለይ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከሚካሄድውን ምርጫ ጋር በተያያዘ ውጥረቱ ተባብሶ መቀጠሉን የገለጹት እማኞች፥ ከተገደሉት አምስት ሰዎች በተጨማሪ ሁለት ነዋሪዎች ከባድ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ለህክምና ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።
በወረዳው የሚገኙ የእርሻ መሬቶች ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በሚል ሰበብ ነዋሪዉን በማፈናቀል ለባለሀብቶች የሚሰጠው ውሳኔ በነዋሪዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያሥነሳ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በቅርቡ መሬታቸውን ለፖለቲከኛ ሹመኞች መሰጠቱን በተቃወሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ መንግስት የተቀነባበረ ጭፍጨፋን ማከናወኑን ነዋሪውች ይገልጻሉ ።
በአዲስ መልክ በጎደሬ ወረዳ ሜጢ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ግጭት አስመልክቶ ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግስት የተስጠ ምላሽ የለም።