በጋምቤላ በሙርሌ ጥቃት ከተጠለፉት ህጻናት መካከል 55 የሚሆኑት እስካሁን አልተለቀቁም

ኢሳት (ሃምሌ 21 ፥ 2008)

በሚያዚያ ወር በጋምቤላ ክልል በደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት ታፍነው ከተወሰዱ ህጻናት መካከል 55 የሚሆኑት አሁንም ድረስ አለመለቀቃቸው ተገለጠ።

የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ሱዳን መንግስት በበኩሉ ሊካሄድ በነበረው ድርድር ታፍነው ከተወሰዱት ወደ 146 ህጻናት መካከል 91 የሚሆኑት ብቻ መለቀቃቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታውቋል።

በህጻናቱ መታገት ስጋቱን ሲገልጽ የቆየው ድርጅቱ የተለቀቁ ህጻናትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ሲደረግ ከነበረው ጥረት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደግ መቆየቱን አመልክቷል።

በክልሉ ከወራት በፊት በተፈጸመው በዚሁ የታጣቂዎች ድርጊት 208 ኢትዮጵያውያን መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከ20 ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የሃይል እርምጃን ለመውሰድ ወታደሮችንና ታንኮችን ቢያሰማራም፣ በታጣቂ ሃይሎ ላይ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድ መቅረቱ የሚታወስ ነው።

ይሁንና፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ባለስልጣናት ከጎሳ ታጣቂዎች ድርድር እንዲያደርግ በማግባባታቸው ታጣቂ ሃይሉ አፍኖ ከወሰዳቸው ወደ 146 ህጻናት መካከል 91 የሚሆኑት በሶስት ዙር ሊለቀቁ ችለዋል።

ታጣቂ ሃይሎ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ 55 የሚሆኑ ህጻናትን ያልለቀቀ ሲሆን፣ ህጻናቱ ያሉበት ሁኔታም ሊታወቅ አለመቻሉም ታውቋል።

የደቡብ ሱዳኑ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወደ ጋምቤላ ክልል በመዝለቅ ጥቃቱን ለምን እንዲወሰድ ታጣቂ ሃይሉም ሆነ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግታት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።