በጋምቤላ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል የተባሉ ዘጠኝ የክልሉ ስራ አስፈጻሚዎች ከሃላፊነት እንዲነሱ ተደረገ

ኢሳት (የካቲት 1 ፥ 2009)

የጋምቤላ ክልል ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ያላቸው ዘጠኝ የክልሉ ስራ አስፈጻሚዎች ከሃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ረቡዕ አስታወቀ።

የክልሉ የትምህርት ቤት ሃላፊ የነበሩት ቱት ጆክን ጨምሮ የክልሉ መስተዳደር የአስተዳደርና ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ምክትል ኤዲተር፣ በጤናና በተለያዩ ከፍተኛ ቦታ ላይ የነበሩት ሃላፊዎች ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ተብለው መባረራቸውን የክልሉ መንግስት ለመገኛኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ይሁንና ለአመታት ሲያገለግሉ የነበሩት እነዚሁ የስራ አስፈጻሚዎች በምን መንገድ ለሃላፊነት ታጭተው እንደነበር የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

የጋምቤላ ክልል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ግለሰቦቹ ወደፊት በህገ እንደሚጠየቁ ቢያሳውቁም የስራ አስፈጻሚዎቹ ምን አይነት የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ እንዳቀረቡ ከመግለጽ ተቆጥቧል።

በመንግስት ተቋማት የሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚይዙ ሃላፊዎች መበራከትን ተከትሎ በጋምቤላ ክልል ብቻ የ328 ግለሰቦች የትምህርት ማስረጃ ማጣሪያ እየተደረገበት መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ይሁንና በፌዴራል ደረጃ ተመሳሳይ ችግር መኖሩ በተለያዩ አካላት ሲጋለጥ ቢቆይም እስካሁን ድረስ የተወሰደ ዕርምጃ የሌለ ሲሆን፣ በከፍተኛ የስልጣን ቦታ ያሉ የመንግስት ሃላፊዎች የዚሁ ሰለባ መሆናቸው ይገለጻል።