በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ኪሎግራም ኮኬይን ስታዘዋውር የነበረች የቤንዙዌላ ተወላጅ በቁጥጥር ስር ዋለች

ኢሳት (የካቲት 1 ፥ 2009)

የካምቦዲያ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ኪሎግራም ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ እፅ ስታዘዋውር የነበረች የቤንዙዌላ ተወላጅ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ረቡዕ አስታወቁ።

ኔሊን ኮሮሞቶ የተባለችው ተጠርጣሪ አደንዛዥ እፁን ከብራዚል መዲና ሳኦ ፓሎ ከተማ ከተቀበለች በኋላ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ታይላንድ ማሸጋገሯን የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች ዋቢ በማድረግ ዘ-ካምቦዲያ ዴይሊ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

የ27 አመቷ ተጠርጣሪ አደንዛዥ እፁን ታይላንድ ካጓጓዘች በኋላ ወደኮሎምቢያ ለማስገባት ስትሞክር በሃገሪቱ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በቁጥጥር ስር መዋሏን ኢን ሶንግ የተባሉ የካምቦዲያ የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር የአደንዛዥ እፅ መምሪያ ሃላፊ ለጋዜጣው አስረድተዋል።

ተጠርጣሪዋ አደንዛዥ እፁን በቁልፍ ቅርጽ በማስመሰል በሻንጣዋ ለማሳለፍ ብትሞክርም የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ቁልፎቹ ከተለመደው መጠን በላይ ሆኖ በመገኘታቸው ተጠራጥረው ፍተሻ በማካሄዳቸው አደንዛዥ እፁ ሊደርስበት መቻሉ ተመልክቷል።

ይሁንና ከ200ሺ ዶላር በላይ የተገመተው አደንዛዥ እፁ በምን ሁኔታ በኢትዮጵያ በኩል ሊዘዋወር ኣንደቻለ የኮሎምቢያ ባለስልጣናት ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

የቬንዙዌላ ዜጋ አደንዛዥ እፁን ከካምቦዲያ በሚገኝ አንድ የመዝናኛ ስፍራ ለጊዜው ማንነቱ ላልታወቀ ሰው ለማድረስ እቅድ እንደነበራት የካምቦዲያ የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች አክለው ገልጸዋል። ይሁንና ለምርመራ ሲባል የተቀባዩ ማንነት ይፋ እንደማይደረግ ባለስልጣናቱ ለጋዜጣው አስረድተዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ የመንግስት ባለስልጣናት የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ከወራት በፊት አንድ ናይጀሪያዊ በሆዱ ውስጥ ደብቆ አደንዛዥ እፅ ለማሳለፍ ያደረገው ሙከራ በፖሊስ ሊደረስበት መቻሉን አየር መንገዱ ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።