(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 9/2011) በጉፋ ዞን በባስኬቶ ልዩ ወረዳና በመሎ ወረዳ የተፈናቀሉ 37ሺ የሚሆኑ ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
እነሱ እንደሚሉት ከሆነ በሁለቱ ወረዳዎች አመራሮች መካከል በቀበሌ ይገባኛል ጥያቄ የተነሳው ግጭት በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
በዚህ ግጭት የ11 ቀበሌዎች ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ማንም የሚደርስላቸው አካል ባለማግኘታቸው በረሃብ እየሞቱ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ለኢሳት ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
ስምንት ወራት ያህል አስቆጥሯል ያላሉ የባስኬቶ ልዩ ወረዳና የመሎ ወረዳ ነዋሪዎች ከቀያቸው ከተፈናቀሉ።
መፈናቀሉ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ደግሞ የተፈናቃዮቹን ቁጥር ወደ 37ሺ እንዲያሻቅብ አድርጎታል ይላሉ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ተመስገን ጌታቸው።
እንደ እሳቸው አባባል ከሆነ ለዜጎቹ መፈናቀል ምክንያቱ የየወረዳዎቹ አመራሮች የሚያነሷቸው የቀበሌዎች የእኔነት ጥያቄ ነው ይላሉ።
ከዚህ የእኔነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ነው በርካቶች ቀያቸውን ለቀው ለከፋ ችግር እንዲጋለጡ የተዳረጉት ያለን ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ የሆነው ጎዳናው ማናዬ ነው።
ጎዳናው ማናየ እንደሚለው የነዚህ አመራሮች የእኔ ነው ጥያቄ የ11 ቀበሌዎች ነዋሪን ከቀዬው ለማፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
ተፈናቃዮቹ ስለደረሰባቸው ችግር እስከ ክልል ድረስ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጆሮ ሰቶ የሚያዳምጣቸውና ለችግራቸው መፍትሄ የሚሰጥ አካል አላገኙም ብሏል።
አቶ ጎዳናው እንደሚለው ዛሬ ላይ ለከፋ አደጋ የተጋለጡትንና ወደ ሆስፒታል የገቡትን ሕጻናት በተንቀሳቃሽ ምስል በታገዘ ማስረጃ አቅርበው መፍትሄ እንዲሰጣቸው ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም።
በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የሚመለከተው አካል ለነዚህ ወገኖች በአስቸኳይ የማይደርስ ከሆነ አደጋው ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል ብለዋል ነዋሪዎቹ።
ኢሳት መረጃውን ይዞ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ደቡብ ክልል አመራሮች በተደጋጋሚ ቢደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።