በጉጅና በጌዲዮ መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ትናንት ምሽት ብቻ በቡሌ ሆራ ከተማ ከ10 በላይ ሰዎች ተገደሉ።
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 08 ቀን 2010 ዓ/ም) የተለያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ሰሞኑን በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት ብቻ ከ10 በላይ ሰዎች በጩቤ ተገድለዋል። በአካባቢው ብቻ እስካሁን የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ20 ይበልጣል።
ከ15 በላይ መኪኖች ስደተኞችን ይዘው በከተማው አስተዳደር ተጠልለው የቆዩ ቢሆንም፣ የክልሉ መስተዳደር ወደ አካባቢያቸው ወስደዋል። የሆስፒታል ምንጮች እንደገለጹት ቆሰለው ሆስፒታል የተኙ 4 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ታርደው መሞታቸውንም ገልጸዋል።
ግጭቱ ተባብሶ የከተማው ህዝብ ወደ ውጭ መውጣትና መግባት አይችልም። ገደብ ገርባ አካባቢ ከፍተኛ ባለው ግጭትም ባለፉት ሁለት ቀናት ከ 10 በላይ ሰዎች እንደሞቱ እጅግ ብዙቁጥር ያላቸዉ እንደቆሰሉና እንደተፈናቀሉ ባጠቃላይ አከበባቢዉ የጦር ቀጠና አንደሚመስል መንግስት ጆሮዳባ ልበስ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ግጭቱ በተነሰባቸው አካባቢዎች ቁጥሩን ለመግለጽ የሚዳግት ህዝብ እንዳለቀ የሚገለጹት ነዋሪዎች፣ በርካታ ቤቶችና ንብረትም ወድሟል። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች በሩዋንዳ የሰማነው ዘግናኝ ግጭት በአገራችን ተከስቶ እያየነው ነው በማለት ተናግረዋል።
ኢሳት ለሚዲያ የማይውሉ አሰቃቂ የግድያ ፎቶግራፎች ደርሰውታል።
በጉጂና በጊዲዮ ማህበረሰቦች መካከል የተነሳው ግጭት ሆን ተብሎ እንደተቀሰቀሰ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ጊዲዮዎች ወደ ደቡብ ክልል እንዲካለሉና በቋንቋቸውም እንዲማሩ ጥያቄ አቅርበዋል የሚል ወሬ መሰራጨቱ ለግጭቱ መንስኤ ሆኗል። ለጌድዮዎች ደግሞ ጉጂዎች ሊጨፈጭፉዋችሁ ነው የሚል መልዕክት እንደተነገራቸው ታውቋል። እስካሁን ከ100 ሺ በላይ የጌዲዮ ተወላጆች ተፈናቅለዋል።
በሌላ በኩል በቡሌ ሆራ ከተማ ትናንት አንድ ወጣት በአጋዚ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል። ወጣቱ ከወንድሙና ከአባቱ ጋር በመሆን የወታደሮች ካምፕ በሚገኝበት አካባቢ እያለፈ እያለ፣ ወታደሮች በቀጥታ በመተኮስ ሲገድሉት አባቱና ወንደሙ ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል።