በጉጂ ተወላጆች እና ጌዲዮ ብሔረሰቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከ10 በላይ ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 8/2010) ባለፈው ሳምንት በደቡብ ኢትዮጵያ በጉጂ ተወላጆች እና ጌዲዮ ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ ትናንት ምሽት ከ10 በላይ ሰዎች ተገደሉ።

ግድያው  እየተካሄደ ያለው  ቡሌ ሆራ ወይንም ሃገረ ማርያም  በተሰኘችው ከተማ ሲሆን በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች  አስክሬን ዛሬ በሆስፒታል እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በዚህም በግጭቱ እስካሁን የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ30 በላይ ደርሷል።

ግጭቱ በመስፋት አጎራባች የሆኑ ብሄረሰቦችም እየተቀላቀሉ መሆኑ ታውቋል።

መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ቢገባም ግጭቱን ለማብረድ እንዳልተንቀሳቀሰ  ይነገራል።

ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች መሰደዳቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ግጭቱ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል። ከስለት መሳሪያ ጀምሮ ቀላል የጦር መሳሪያዎች በጥቅም ላይ በዋሉበት ግጭት እስከሁን ከመጣበት ይልቅ በቀጣይ የሚሆነው ትልቅ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን ከአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች አመልክተዋል።

በጌድዮና በጉጂ መሃል የተጀመረው ይህው ግጭት መብረድ ሳይችል የሰው ልጅ ህይወት በመቅጠፍ ላይ ነው።

የኢሳት ምንጮች ከአካባቢው ካደረሱን መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው በግጭቱ እስከአሁን ከ30 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ከቅዳሜ ጀምሮ በቀርጫ ወረዳ በርካታ ቤቶች እየተቃጠሉ ሲሆን በበርካታ ቀበሌዎችም ውደመት መከትሉን ለማወቅ ተችሏል።

እስከቅዳሜ ድረስ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 20 እንደነበረ የገለጹት የኢሳት ምንጮች በትላንትናው ዕለት ምሽት ከ10 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

የትላንት ምሽቱ ግድያ ቡሌ ሆራ ወይም ሀገረማርያም በተሰኘች ከተማ የተፈጸመ መሆኑ ታውቋል።

ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን ይችላል።

በዛሬው ዕለት በርካታ አስከሬኖች በቡሌ ሆራ ሆስፒታል እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በዚህም ከአንድ ሳምንት በላይ በዘለቀው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ከ30 በላይ ደርሷል።

እንደምንጮቻችን ዘገባ ኤላፈርዳ የምትባለው ከተማ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየነደደች ነው።      በግጭቱ ምክንያት አከባቢውን ለቀው የተሰደዱ ሰዎች ቁጥርም 40ሺህ መድረሱ ታውቋል።

የቀርጫ ወረዳ በጉጂ ዞን ከሚገኙ ቡና አብቃይ ወረዳዎች አንዷ ስትሆን በወረዳዋ በርካታ የጌድዮ ብሔረሰብ ተወላጆች የቡና መፈልፈያና መቀሸርያ ቦታ እንዳላቸው የጠቀሱት ምንጮች እነዚህ ቦታዎች የጥቃቱ ኢላማ ሆነው በመውደም ላይ ናቸው።

በሌላ በኩል የግጭቱ አድማስ ሰፍቶ  ሁኔታው አስከፊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የኢሳት ምንጮች ትላንት በአካባቢው የደረሱት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግጭቱን ለማስቆም የወሰዱት ርምጃ አለመኖሩን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ኮማንድ ፖስቱን ጨምሮ የመንግሥት አካላት ምንም ዓይነት ርምጃ መውሰድ አልቻሉም።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት የደረሱት ዘግይተው ቢሆንም ከደረሱም በኋላ ማስቆም ሳይችሉ በተለይ በቀርጫ ከተማ የመከላከያ ሰራዊት ባለበት በተኩስ እሩምታ የታገዘ ጭፈራና መጤ ተብሎ በተለየው ኢትዮጵያዊ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ከአካባቢው ነዋሪዎች የደረሰን መልዕክት ያስረዳል።

ወደ ጉጂና ጌዲዮ ዞኖች፣ እንዲሁም ወደ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ስልክ በመደወል ስለጉዳዩ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።