በጉጂ ዞን ንግድ ባንክ ስራ በማቆሙ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ መውሰድ አልቻሉም

ጥቅምት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የመንግስት ሰራተኞች ለኢሳት እንደገለጹት በቀድሞዋ ክብረመንግስት በአሁኑ አዶላ ወዮ ከተማ የሚገኘው ክብረመንግስት የኢትጵያ ንግድ ባንክ ካለፉት 9 ቀናት ጀምሮ ስራ በማቆሙ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ለመውሰድ ተችግረዋል። ቤተሰቦቻችን ለችግር ተዳርገዋል የሚሉት ሰራተኞች፣ አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ የኔትወርክ ችግር ነው ጠብቁ ከመባል ውጭ መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም። ፖሊሶችን ጨምሮ ሁሉም የመንግስት ስራተኞች ደሞዛቸው በንግድ ባንክ በኩል በተከፈተ አካውንት የሚገባላቸው ሲሆን፣ ደሞዛቸውን መውሰድም ሆነ ገንዘባቸውን ለማውጣት ባለመቻላቸው ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ ወድቀዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የባንኩን ሃላፊዎች ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።