በየመን በተከሰተ አውሎ ንፋስ ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ

ጥቅምት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በምህጻረ ቃል UNHCR ዛሬ ከዋና ጽሕፈት ቤቱ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ እንዳስታወቀው በየመን ነፋስና ቀላቅሎ በጣለው ኃይለኛ ዝናብ ሳቢያ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ሶማሊያዊያንና የኤርትራ ዜጎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
በሳኡዲ አረቢያ የሚመራው የጥምረት ጦርና አገሪቱን ተቆጣጥረው የነበሩት በኢራን የሚደገፉት የሃውቲ አማጽያን መሃከል በሚደረገው ውጊያ ሳቢያ የመን ሰላሟ ከራቃት ዓመታት ያስቆጠረች ስትሆን፣ የአገሪቱ ዜጎች የትውልድ ቀያቸውን በመልቀቅ ወደተለያዩ የዓለም አገራት ሲሰደዱ በአንጻሩ የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች በጦርነት ወደምትታምሰው የመን መነሻቸውን ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻዎች በማድረግ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው መትመማቸውን ያላቋረጡ ሲሆን አብዛሃኞቹ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መሆናቸውም ተገልጿል።
በየመን ከጦርነት በተጨማሪ የተፈጠረው አሳሳቢ የተፈጥሮ አደጋ ሁኔታዎችን ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረጋቸውና ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ እያደር እየከፋ መሄዱንና የምግብ፣የመጠለያ አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ በተለይ ሕጻናት አሳሳቢ የሆነ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ አሳስቧል። አሁንም አዲስ መጪ ስደተኞች ባሕር እያቋረጡ ወደ የመን መፍለስ መቀጠላቸውንም ድርጅቱ በሪፖርቱ ገልጿል።
በተጨማሪም ቁጥራቸው 387 ከሚሆኑ በማላዊ እስርቤት ሲንገላቱ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ውስጥ 50 ዎቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጁቱን ማጠናቀቁንና ከእነዚህ ውስጥ 15 ያህሉ ሕጻናትና ታዳጊዎች እንዳሉበት ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም አስታውቆ ቀሪዎቹ በአሳሳቢ አያያዝ የተያዙ መሆኑንም አክሎ ገልጿል።
ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ስደተኞችን ለማገዝ የተደረገ ምንም ዓይነት ሙከራ አለመደረጉ በስደተኞቹና በቤተሰባቸው ላይ ቅሬታን ፈጥሯል።ዜጎች ከአገራቸው ተሰደው ለሚደርስባቸው ስቃይ የኢትዮጵያ ኤንባሲዎች ምላሽ ያለመስጠት አሰራሮች በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በተደጋጋሚ መከሰቱ የሚታወስ ነው።