በጉጂና በጌዲዮ ብሄረሰቦች ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 200ሺህ ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2010)በጉጂና በጌዲዮ ብሄረሰቦች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 200ሺህ መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ።

ፋይል

የድርጅቱ የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኦቻ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት ካፈናቀለው ህዝብ በተጨማሪ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ጽሕፈት ቤቱ ለተጎጂዎች ድጋፍ እያደረገ እንደሆነም አስታውቋል።

በግጭቱ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መገለጹ የሚታወስ ነው።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳዮች መስሪያ ቤት ኦቻ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በሚያዚያ 5ቱ ግጭት ከምዕራብ ጉጂና ከጌዲዮ ዞኖች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ደርሷል።

ከእያንዳንዱ ዞን 100 ሺህ ያህል ሰው መፈናቀሉን የገለጸው ሪፖርቱ በአብዛኛው የመፈናቀሉ ሰለባ የሆኑት የጌዲዮ ተወላጆች መሆናቸውን ጠቅሷል።

ከዚህ መጠነ ሰፊ መፈናቀል በተጨማሪ የሰው ህይወት መጥፋቱን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሆኖም ምን ያህል ሰዎች በግጭቱ እንደተገደሉ የኦቻ ሪፖርት በቁጥር አላስቀመጠም።

ኢሳት በተከታታይ ባቀረባቸው መረጃዎች በሁለቱ ወገኖች መሀል በተነሳው ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

በአብዛኛው ህጻናት የግድያው ሰለባ መሆናቸውንም የአካባቢው ነዋሪዎችን እማኝ በማድረግ መዘገባችን የሚታወስ ነው።

ለዘመናት አብረው ተዋልደውና ቤተሰብ መስርተው በሚኖሩት ኢትዮጵያውያን መካከል እንዲህ ዓይነት ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲፈጠር ያደረገው አሁን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የሚከተለው ፖሊሲ መሆኑን ኢሳት ያነጋገራቸው ሁለቱም ወገኖች ገልጸዋል።

በካድሬዎች ጠንሳሽነት ወጣቱን እያስተባበሩ ግጭቱን የሚያባብሱት የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት መሆናቸውም ታውቋል።

በግጭቱ ወቅት የመከላከያ ሰራዊትና የኮማንድ ፖስቱ ታጣቂዎች በአካባቢው የደረሱ ቢሆንም መከላከል እንዳልቻሉ የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

ለሶስት ሳምንት በዘለቀው ግጭት ወቅት ከአገዛዙ በኩል ምንም ዓይነት ርምጃ ያልተወሰደ ሲሆን የመንግስት መገናኛ ብዙሃንም ስለጉዳይ ሽፋን ሳይሰጡ መቆየታቸው እንዳሳዘናቸው ተፈናቃዮች መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ኦቻ በሪፖርቱ እንዳመለከተው በግጭቱ ሳቢያ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከስቷል።

መፈናቀሉ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ሁኔታው የከፋ እንደሆነም ሪፖርቱ ላይ ተገልጿል።

የመንግስታቱ ድርጅት የተፈናቀሉትን ለመርዳት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

ሆኖም ከተፈናቃዩ ብዛት አንጻር የሚደረገው ድጋፍ በቂ አይደለም ሲል ገልጿል።

ተፈናቃዮቹን ወደቦታቸው ለመመለስ ጥረትም እየተደረገ ነው ብሏል።

በሌላ በኩልም በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል ሲል የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ኢሶዴፓ ገልጿል።

ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ የተናገሩት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው ከቤት-ንብረቱ የተፈናቀለዉ ሕዝብ እስካሁን በቂ መጠለያ እና ድጋፍ አላገኘም ብለዋል።

ለሕዝቡ እርዳታ ለማፈላለግም ሆነ በአካባቢዉ ለመንቀሳቀስ የወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዳልፈቀደላቸውም አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።