የአማራ ተወላጆች እንዲገደሉና እንዲፈናቀሉ ያደረገው የቦሎ ዴዴሳ ቀበሌ መስተዳድር መሆኑ ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2010) በቤንሻንጉል ክልል ይኖሩ የነበሩትን የአማራ ተወላጆች እንዲገደሉና እንዲፈናቀሉ ያደረገው በካማሽ ዞን የቦሎ ዴዴሳ ቀበሌ መስተዳድር መሆኑን የሚያረጋግጥ የደብዳቤ ሰነድ ይፋ ሆነ።

የቦሎ ዴዴሳ ቀበሌ መስተዳድር ለአማራ ተወላጆች በሚል በጻፈው ደብዳቤ እስከ መጋቢት 30 ወይንም ሚያዚያ 10/2010 ድረስ አካባቢውን ለቃችሁ ካልወጣችሁ ተገዳችሁ ትለቃላችሁ የሚል ማስጠንቀቂያ መጋቢት 30/2010 መጻፉን ለማረጋገጥ ተችሏል።

ደብዳቤው የአማራ ተወላጆች ሃብትና ንብረታቸውን ሸጠው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ያለበት መሆኑንና ይህን መነሻ አድርጎ ጥቃቱ መፈጸሙን የተጎጂዎቹ ተወካይ አቶ አበባው ጌትነት ለኢሳት ገልጿል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ካማሺ ዞን በቡሎ ዴዴሳ ቀበሌ አስተዳደር ምክትል ሊቀመንበር ንጉሱ ጀርሞሳ ለአማራ ተወላጆች መጋቢት 16/2010 የተጻፈው ደብዳቤ ሰዎቹ አካባቢውን ለቀው ካልወጡ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው ያመለክታል።

እናም የአማራ ተወላጆቹ እስከ መጋቢት 30 ወይንም ሚያዚያ 10/2010 ድረስ ቤንሻንጉልን ለቀው ካልወጡ ተገደው እንደሚወጡ ደብዳቤው ያስጠነቅቃል።

በዚሁም መሰረት ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸውና ከ13 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተፈናቃዮቹ ገልጸዋል።

ምክትል ሊቀመንበሩ ንጉሱ ጀርሞሳ ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ጥቃቶችን በአማራ ተወላጆች ላይ ይፈጸም እንደነበር የተፈናቃዮቹ ተወካይ አቶ አበባው ጌትነት ለኢሳት ገልጸዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የብአዴን ተወካዮች ይህ ስለመፈጸሙ ማረጋገጫ እንዳላቸውም ተወካዩ ገልጸዋል።

ይህ ደብዳቤ ማረጋገጫ ከተገኘ በኋላ ግን የአማራ ክልል ባለስልጣናት ከቤንሻንጉል ተወካዮች ጋር ሆነው ሁኔታውን ለማረጋጋት ከመሞከር ውጭ ለተጎጆዎቹ ካሳም ሆነ በዘላቂነት ለማቋቋም ያደረጉት ጥረት እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል።