ግንቦት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ጉንዶመስቀል ከተማ ሶራ ካፌ ውስጥ 4፡30 አካባቢ በፈነዳ ቦንድ ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ከተጎዱት መካከል 3ቱ ክፉኛ ቆስለው ወደ ፍቼ ሆስፒታል ሲወሰዱ አንዱ ደግሞ በከተማው ጤና ጣቢያ በመታከም ላይ ነው። ከቆሰሉት መካከል አንድ ፖሊስ፣ አንድ ነጋዴና እና ሁለት አርሶአደሮች ይገኙበታል።
የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ መስፍን ፍንዳታው የተከሰተው በግል ጸብ መሆኑን ለኢሳት ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ ወረዳ ከወራት በፊት አንድ የወረዳ የጸጥታ ዘርፍ ሹም የአንዲት አርሶአደርን ሚስት በባሉዋ ላይ ክብረነክ ጉዳዮችን እንደትፈጽም መገደዱዋን እና በሰደፍ በመመታቱዋ ጽንሷ እንዲወርድ መደረጉ በኢሳት ከተዘገበ በሁዋላ የመንግስት ጋዜጠኞች ወደ አካካቢው ወርደው ግለሰቡዋን ማነጋገራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የአካባቢው ነዋሪዎች የተፈጸመውን ድርጊት በዝርዝር ለጋዜጠኞች ማስረዳታቸውን ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ይሁን እንጅ በአቶ በረከት ስምኦን ትእዛዝ እንዲላኩ የተደረጉት ጋዜጠኞች መረጃዎን እስካሁን ይፋ አለማድረጋቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የኢሳት ወኪሎች ገልጸዋል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊው አቶ መስፍን ” በግለሰቡ ላይ አስፈላጊው ማስረጃ ተሰብስቦ ለፍርድ ቤት የቀረበ በመሆኑ፣ የፍርድ ቤቱን የመጨረሻ ውሳኔ እየጠበቁ” መሆኑን ተናግረዋል። የመንግስት ሹሙ ድርጊቱን የፈጸመው በራሱ ተነሳሽነት እንጅ ከመንግስት ጋር በተያያዘ አለመሆኑን ጸጥታ ሹሙ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ሹሙ ድርጊቱን የፈጸመው አርሶአደሩ የደበቀውን መሳሪያ እንዲያወጣ ከጠየቀ በሁዋላ አርሶ አደሩም ” መሳሪያ የለኝም” በማለት መመለሱን ተከትሎ ነው። ጉዳት የደረሰባት ሴት በሆስፒታል ህክምና ሲደረግላት ቆይቶ አሁን በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።