(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2011) በጉራጌ ዞን ማረቆና መስቃን ወረዳዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት የየወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች እጅ አለበት በሚል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉ ተገለጸ።
በክልል ደረጃ በደኢህዴን ውስጥየሚገኙና የግጭቱ ዋና አቀናባሪዎችን ያልነካ እስር ችግሩን አይፈታውም ሲሉ ነዋሪዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።
የደቡብ ክልል ፖሊስ የማረቆ ወረዳ አስተዳዳሪን አቶ በለጠ ደራሮንና የመስቃን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታህ ሸምሱን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ባሳወቀበት መግለጫው ግጭቱን በመቀስቀስና በማባባስ ሚና ያላቸውን አመራሮች በማሰር ላይ መሆኑን ገልጿል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከ40 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ32ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ እንዳስታወቀው በማረቆና መስቃን ወረዳዎች ለተነሳው ግጭት እጃቸው በአንድም ይሁን በሌላ የሚገኝባቸው አመራሮችን በቁጥጥር ስር እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።
በዚህም መሰረት የማረቆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ደራሮንና የመስቃን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታህ ሸምሱን ጨምሮ ሌሎች የወረዳዎቹ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ብሏል የደቡብ ፖሊስ።
ከአስተዳዳሪዎቹ በተጨማሪ የየወረዳዎቹ የጸጥታና ፖሊስ አመራሮችም ተይዘዋል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ግለሰቦች ቁጥር 69 መድረሱንም የደቡብ ክልል ፖሊስ አስታውቋል።
ከመስከረም ወር ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ግጭት ውስጥ በቀጥታ ሲያስተባብሩ ነበሩ የተባሉ የ115 ሰዎች ስም ዝርዝር ተለይቶ የፍርድ ማዘዣ መውጣቱን የገለጸው የደቡብ ክልል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የማዋል ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጿል።
በቀበሌ አስተዳደሮች ይገባኛል መነሻ በተነሳውና የብዙዎችን ህይወትና ንብረት ያወደመው ግጭት ላይ በዋናነት ስማቸው የሚጠቀሱ የደቡብ ክልል አመራር ላይ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋል አለማዋላቸው ግጭቱ እንዲቀጥል ያደርገዋል ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጉራጌ ዞን አንዳንድ አመራሮች ለኢሳት ገልጸዋል።
የግጭቱ ዋና ራስ የሚገኘው በአዲሱ ለውጥ አኩርፈው ያሉና የተገለሉ የክልሉና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ግለሰቦች ሆነው ሳለ ርምጃው በዝቅተኛ አመራር ባሉት ላይ ማተኮሩ ለውጥ አያመጣም ብለዋል።
የየወረዳ አመራሮች በደኢህዴን ውስጥ ከነበሩና አሁንም ግንኙነታቸው የቀጠሉ አመራሮች በሚሰጧቸው መመሪያ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ የተከሰተውን ቀውስ እንደለኮሱትና እንዳባባሱት የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ አለመግባቱን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ቀጠናው የቀውስ እንዲሆን በማድረግ ላይ መሆናቸውን የሚገልጹት ስማቸው እንዲጠቀስ ያለፈለጉ የጉራጌ ዞን አንዳንድ ሃላፊዎች ለግጭቱ ትክክለኛ መፍትሄ ለመስጠት ደኢህዴን ውስጥ ያሉና የነበሩ አመራሮችንም የጨመረ ርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በተከሰተው ግጭት 43 ሰዎች ሲገደሉ 32ሺህ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
አያሌ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት በግጭቱ ምክንያት መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎች ለሳምንታት መቆማቸው የሚታወስ ነው።
በተመሳሳይ በጉራጌና ሀዲያ ዞኖች ወሰን ላይ ባለፈው ሳምንት በተፈጠረ ግጭት 5 ሰዎች መጎዳታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የመንግስት ሃይሎች ግጭቱ ከመስፋፋቱ በፊት በአካባቢው በመድረሳቸው ሊበርድ መቻሉ ተገልጿል።