ሶስት ሃገራት የዲሞክራሲ ርምጃ አሳይተዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 09/2011) በዓለማችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት ሃገራት በ2018 የዲሞክራሲ ርምጃ ማሳየታቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ።

ለዲሞክራሲ እጅግ ፈታኝና አደገኛበሆነውና አምባገነኖች ይበልጥ አፋኝ ሆነው በወጡበት በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂ ሁኔታ ተከስቷል ስትል በዋሽንግተንፖስት ላይ ጽሁፏን ያቀረበችው ፍረዳ ጊቲስ በትግራይ የበላይነት ስር የቆየው ዘረፋና ስርዓት በዚህ ዓመት ማብቃቱን አመልክታለች።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት በውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ የለውጥ ስሜት መቀስቀሱን ትናንት ዋሽንግተን ፖስት ላይ የወጣው  ጽሁፍ ያስረዳል።

በአሜሪካውያን ዘንድ ታዋቂና ተነባቢ በሆነው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ ትናንት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 17/2018 ጽሁፏን ያቀረበችው ፍረዳ ጊትስ 2018 አምባገነኖች ይበልጥ አፋኝ ሆነው መውጣታቸው በሃንጋሪ፣ ኒካራጓና ፍሊፒንስ በመሳሰሉት ሃገራት መታየቱን ገልጻለች።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ፣ ሩማንያና ፔሩ የዲሞክራሲ ርምጃ በማሳየት ተስፋ ሰጪ ጉዞ ላይ መሆናቸውን ዘርዝራለች።

ከዋሽንግተን ፖስት በተጨማሪ በሲ ኤን ኤን ግሎባል አፌየርስ ላይ ዓለም አቀፋዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን የምትተነትነው ፍረዳ ጊትስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ትልቁ አስደናቂ የዲሞክራሲ ርምጃ የታየው የ100 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ ነው ስትል ገልጻለች።

በፍጹም የአፈና ስርዓት ውስጥ በቆየችውና ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች የበረከቱባት ኢትዮጵያ ስደት የደህንነት ዋስትና ሆኖ መቆየቱን አስታውሳለች።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ ስልጣንን በዋናነት ይዞ አይን ባወጣ መንገድ ያለ ይሉኝታ የትግራይ ተወላጆችን የተለየ ተጠቃሚ ሲያደርግ የነበረውና ተቃዋሚዎችን እያፈነ በዘረፋ ውስጥ የቆየው ከትግራይ የወጣው ቡድን በድርጅቱ ውስጥ በተካሄደው እንቅስቃሴ በመጋቢት ወር ከስልጣን መወገዱን በዋሽንግተን ፖስት ላይ በጻፈችው ፈረዳ ጊትስ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መውጣት ለዲሞክራሲው ዕመርታ አስተዋጽኦ ዘርዝራለች።

በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች መለቀቃቸውን ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት የሆነውን ሲ ፒ ጄን በመጥቀስም ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ከጋዜጠኞች ውጭ ሆነው መገኘታቸውን ገልጻለች።

ከ20 ዓመታት በላይ ከኤርትራ ጋር የነበረው ውዝግብ ማብቃቱንና በውጭ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውን ዋሽንግተን ፖስት ላይ የቀረበው የፍረዳ ጊትስ ጽሁፍ በማስረጃነት ያሳያል።

ወደ አሜሪካ በተጓዙበት ወቅት በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጀግና አቀባበል እንደተደረገላቸው የገለጸችው ፍረዳ ጊትስ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ የገቡትንም ቃል አስታውሳለች።

በኢኮኖሚ ቀውስና በጎሳ ግጭት የምትናጥ ሃገርን የመሪነት መንበር የተቀበሉት ዶክተር አብይ አህመድ ከመከራው በተቃራኒ እጅግ ከፍተኛ ድጋር ያገኙ መሪ መሆናቸውንም ገልጻለች።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ አርመንያና ፔሩ በተስፋ ሰጪ የዲሞክራሲ ጎዳና ላይ መሆናቸውንም ከዋሽንግተኝ ፖስቱ ዘገባ መረዳት ተችሏል።